መግቢያ
1
ምስጢረ ጥምቀት
መግቢያ
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስን “እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” ብሎ እንደተናገረው ከውኃና ከመንፈስ ተወልደን የሥላሴን ልጅነት የምናገኝበት መንግሥተ ሰማያት የምንገባበት ኃጢአታችን የሚደመሰስበት ድኅነትን የምናገኝበት ዐቢይ ምሥጢር ነው /ዮሐ. 3፥5/፡፡ ጥምቀት በምሥጢረ ሥላሴና በምሥጢረ ሥጋዌ አምኖ ለሚፈጽመው ሰው ሁሉ ለኃጢአት መደምሰሻ ከሥላሴ የጸጋ ልጅነት ለመቀበልና የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የተሰጠ ልዩ የሕይወት መንገድ ነው፡፡ ጥምቀት በጽርዕ ቋንቋ ኤጲፋኒያ በግእዝ አስተርዮ በአማርኛ መገለጥ ይባላል፡፡ ቃሉ በቀጥታ ሲተረጎም በውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት፣ መነከር፣ መዘፈቅ፣ መጥለቅ ማለት ነው፡፡ ጥምቀት ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን (ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ሜሮን፣ ምሥጢረ ቁርባን፣ ምሥጢረ ንስሐ፣ ምሥጢረ ክህነት፣ ምሥጢረ ተክሊል፣ ምሥጢረ ቀንዲል) አንዱ ነው፡፡
የጥምቀት አመጣጥ
የምሥጢረ ጥምቀት መሥራች ራሱ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ነገር ግን ከጌታችን ጥምቀት በፊት አይሁድ ለመንጻትና ለኃጢአት ሥርየት (ይቅርታ) የሚጠመቁት ጥምቀት ነበራቸው፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር በረድኤት የሚገለጥባቸው የተቀደሱ ዕለታትና ቦታዎች ሁሉ ሰውነትንና ልብስን ማጠብ የእግዚአብሔር ቤት ማገልገያ የሆኑ ዕቃዎችን ሁሉ ማጠብ ማንጻት ሥርዓትና ልማድ ነበር፡፡ የእግዚአብሔርም ፈቃድ ያለበት አሠራር ነበር፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቤት ከመቅረባቸውና ለተቀደሰው አገልግሎት ከመግባታቸው አስቀድመው እግሮቻቸውንና እጆቻቸውን የመታጠብ ግዴታም ነበራቸው፡፡ ሰውነታቸውን ከአፍአዊ (ከውጫዊ) እድፍ በማጠብና ንጹሕ በማድረግ በባሕርይ ንጹሕና ቅዱስ በሆነው አምላክ ፊት ውስጣዊ ሕይወትን ንጹሕ አድርጎ የመቅረብን ሥርዓትና ምሥጢር የሚያመለክት ልማድ ነበር፡፡
የጥምቀት ምሳሌዎች
አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ መልከጼዴቅ መሔዱ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም የምእመናን መልከጼዴቅ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ናቸው፡፡ /ዘፍ. 14፥17/
ኢዮብ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ተፈውሷል፡፡ ይህም ምእመናን ተጠምቀው ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ የመፈወሳቸው ምሳሌ ነው፡፡
ንዕማን ሶርያዊ ተጠምቆ ከለምጽ ድኗል፡፡ /2ነገ. 5፥14/ ይኸውም ምእመናን ተጠምቀው ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ የመዳናቸው ምሳሌ ነው፡፡
የኖኅ መርከብ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ. 6፥13 ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍሳት በውኃ የዳኑባትን መርከብ ሲሠራ በኖኅ ዘመን የእግዚአብሔር ትዕግሥት በዘገየ ጊዜ ቀድሞ ክደውት ለነበሩት ሰበከላቸው፡፡ አሁንም እኛን በዚያው አምሳል በጥምቀት ያድነናል ሥጋን ከዕድፍ በመታጠብ አይደለም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመነሣቱ በእግዚአብሔር እንድናምን መልካም ግብርን ያስተምረን ዘንድ ነው እንጂ” /1ጴጥ. 3፥20/
ለአብርሃም ሕግ ሆኖ የተሰጠው ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም ከአረጀ በኋላ ቢገረዝም ልጆቹ ግን በተወለዱ በስምንተኛው ቀን እንዲገረዙ እግዚአብሔር አዞ ነበር /ዘፍ. 17፥9/ “በሰው እጅ የአልተደረገ መገረዝን በእርሱ ሆናችሁ ተገረዛችሁ፡፡ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችኋል በእርስዋም ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትና በሃይማኖት ከእርሱ ጋር ተነሥታችኋል” /ቈላ. 2፥11/
ጌታችን ለምን ተጠመቀ?
-
የዕዳ ደብዳቤያችንን ለመደምሰስ
አዳምና ሔዋን ፍዳው በፀናባቸው መከራው በበዛባቸው ጊዜ የሚያቃልልላቸው መስሏቸው ዲያብሎሰ ስመ ግብርናችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ ባላቸው ጊዜ አዳም ገብሩ ለዲያቢሎስ (አዳም የዲያብሎስ የወንድ አገልጋይ) ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ (ሔዋን የዲያብሎስ ሴት አገልጋይ) ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡ ዲያብሎስም ይህንን ደብዳቤ አንዱን በሲኦል አንዱን በዮርዳኖስ አስቀመጠው፡፡ በዮርዳኖስ ያስቀመጠውን ጌታችን ሲጠመቅ እንደሰውነቱ ረግጦ ደምስሶታል፡፡ ይህንን ጽሕፈት ለመደምሰስ ነው ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀው፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው” ያለው /ቆላ 2፥14/፡፡
- ምስጢረ ሥላሴን ለመግለጥ
ጌታችን በፈለገ ዮርዳኖስ ሲጠመቅ ምስጢረ ሥላሴ ግልጽ ሆኗል፡፡ አብ በደመና “የምወደው የምወልደው ልጄ ይህ ነው” በማለቱ አብ የወልድ አባት መሆኑ ታወቀ፡፡ መንፈስ ቅዱስም የባሕርይ ሕይወቱ መሆኑን ሲያስረዳ በአምሳለ ርግብ በራሱ ላይ ተቀመጠ ወልድም በተለየ አካሉ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ታየ፡፡ ስለዚህ ምሥጢርን ለመግለጥ ስንል የአንድነት የሦስትነት ምስጢር በጐላ ሁኔታ እንዲታወቅ ተጠመቀ ማለት ነው፡፡ /ማቴ. 3፥16/
-
ትንቢቱን ለመፈጸም
“አቤቱ ውሆች አዩህ፣ ውሆችም አይተውህ ፈሩ ጥልቆች ተነዋወጡ ውሆችም ጮኹ፡፡” ተብሎ በቅዱስ ዳዊት የተነገረውን ትንቢት ለመፈጸም ተጠመቀ /መዝ 77፥16/፡፡ጌታችን መቼ ተጠመቀ?ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በ5531 ዓመተ ዓለም ዘመነ ሉቃስ ማክሰኞ ጥር 11 ቀን ከሌሊቱ በ10ኛው ሰዓት ነበር፡፡ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 19 በተጠመቀም ጊዜ ዕድሜው 30 ዓመት ከ13 ቀን ነበር፡፡ /ሉቃ. 3፥23/በብሉይ ኪዳን ሥርዓትና ልማድ ካህናት ለቤተ እግዚአብሔር ተልእኮ እና መንፈሳውያን አገልግሎቶች ከ30 ዓመት ዕድሜ በፊት አደባባይ አይወጡም ነበር፡፡ እጅግ አስፈላጊ እንኳ ቢሆን ከ20 እና 25 ዓመት አስቀድሞ ለአገልግሎት መሰየም ልማድ አልነበረም፡፡
የቤተ እግዚአብሔር አገልጋዮች በዕድሜና በዕውቀት የበሰሉ፣ በጠባይና በሥራ ልምድ የተፈተኑ ተልዕኳቸውን በብቃት ለመወጣት በተገልጋዩ ሕዝብ ዘንድ የተመሰከረላቸው መሆን ነበረባቸው፡፡ /ዘጸ. 4፥3፤1ዜና መዋ. 23፥24፤ 1ጢሞ. 3፥6-10/ ያንን ሥርዓት ለመፈጸም ጌታችን የተጠመቀውና ለትምህርተ ወንጌል የተገለጠው በ30 ዓመቱ ነበር፡፡ ዮሐንስ መጥምቅም የጌታን መምጣት ለማወጅ በዮርዳኖስ ይሁዳ ምድረ በዳዎች ወጥቶ የታየው ከ30 ዓመት ዕድሜው በኋላ ነው፡፡
ሌላው ዐቢይ ምክንያት የሰው ሁሉ መጀመሪያ አዳም የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ተፈጥሮ በ40ኛ ቀን ተሰጥቶት ኋላም በኃጢአት ምክንያት ያስወሰደውን ልጅነት ለማስመለስ ነው፡፡ ክርስቶስ የተጠመቀው ክብር ሽቶ ሳይሆን የአብ የባሕርይ ልጅነቱን (የባሕርይ አምላክነቱን) ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ለማስመስከር፣ ውኃውን ለመቀደስ፣ የአዳምን ልጆች የእዳ ደብዳቤ ለመደምሰስና በስህተት የጠፋውን የልጅነት ክብር ለመመለስ ነው፡፡ ጌታ ተጠምቆ ከውኃው ከወጣ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ በማረፍ አብ በደመና “ይህ ልጄ ነው” ብሎ ሲመሰክርለት ምሥጢረ ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በጉልህ ተረጋግጧል፡፡ /ማቴ. 3፥16/
የጌታችን ጥምቀት በዮርዳኖስ
በኢየሩሳሌም አካባቢ ብዙ ወንዞች ኩሬዎችና ሐይቆች መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ ጌታ ጥምቀቱን በዮርዳኖስ ያደረገው ስለዚሁ አስቀድሞ የተነገረውን ትንቢት መፈጸሙን ለማረጋገጥ ነው፡፡ “ባሕር አይታ ሸሸች ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ” /መዝ. 113፥3/ ከዚህም ጋር ከላይ ምንጩ አንድ የሆነው ዮርዳኖስ ዝቅ ብሎ በደሴት ተከፍሎ እንደገና እንደሚገናኝ በግዝረት በቁልፈት (በመገዘርና ባለመገዘር) ተለያይተው የነበሩ ሕዝብና አሕዛብ መላው የአዳም ልጆች በጌታችን ጥምቀት አንድ መሆናቸውን የሚገልጽ ትርጉም አለው፡፡ እስራኤል ዮርዳኖስን ተሻግረው ምደረ ርስት ገብተዋል፡፡ ያመኑ የተጠመቁ ምዕመናንም በጥምቀት ገነት መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ፡፡ ሌላው በዮርዳኖስ ተጥሎ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤ ይደመስስልን ዘንድ /ቈላ. 2፥14/
2
ምሥጢረ ሜሮን
መግቢያ
ሜሮን ቅባት ማለት ሲሆን ለመንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ የሚውል የተቀደሰ ቅባት ነው ። የተለያየ መዓዛ ከሚሰጡ ዕፀዋት ተቀምሞና ተነጥሮ ይዘጋጃል ።
በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩ ካህናት የሚሾሙት ፤ ነገሥታት የሚግሡት ፤ የተቀደሰ ቅብዓ ክህነትናቅብዓ መንግሥት እየተቀቡ ነበር ። ዘፀ 28፥41 ። ዘፀ 29፥7 ፤ ዘሌ 4፥3 ። ዘሌ 6፥20 ። ዘሌ 8፥2 ። 1ሳሙ 9፥16 ። 1ሳሙ 16፥1 ። 1ነገ 1፥34። በዚህ የብሉይ ኪዳን ዘመን ካህናቱም ሆኑ ነገሥታቱ የሚቀቡት ከእስራኤል ዘሥጋ መካከል ተመርጠው የእግዚአብሔርን ህዝብ ለማገልገል ሲሆን ፤ ቅብዓ ክህነቱም ሆነ ቅብዓ መንግስቱ አገልግሎታቸውን በማስተዋልና በታማኝነት እንዲፈጽሙ የሚያተጋቸው የእግዚአብሔር ፀጋ የሚተላለፍበት መንገድ ነው ። በዚህ ዓይነት የመሪነት ቦታ የያዙ ካህናትና ነገሥታት ከእግዚአብሔር የሚሰጣቸውን ትእዛዝ በመቀበል ለእግዚአብሔር እየታዘዙና ህዝባቸውን በቅንነት እያገለገሉ አልፈዋል ።
ቅብዓ ሜሮን በሐዲስ ኪዳን
በብሉይ ኪዳን ለታላቅ መንፈሳዊ አገልግሎት ይውል የነበረው የተቀደሰ ቅብዓት በሐዲስ ኪዳንም መንፈሳዊ ዓላማውን ሳይለቅ አገልግሎቱ ቀጥሏል ። 1 ዮሐ 2፥17። ቅብዓ ሜሮን ከተለያዩ ዕፀዋት ከተቀመመ በኋላ በሊቀ ዻዻስና በዻዻሳት ጸሎትና ቡራኬ ይባረካል።
የቅብዓ ሜሮን አገልግሎት
ሐዋርያት በጸሎተ ሐሙስ ማታ በህጽበተ ዕግር አማካኝነት ተጠምቀዋል ። ዮሐ 13 ፥ 4 ። መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት ግን ጌታችን ባረገ በሀምሳኛው ቀን ነበር ። የሐ ሥ 2፥1 ። በሐዋርያት ዘመን የነበሩ ምዕመናንም አምነው ከተጠመቁ በኋላ እጃቸውን ሲጭኑባቸው መንፈስ ቅዱስ ይወርድላቸው ነበር ። የሐ ሥ 8፥14 ። ጌታችን ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በራሱ ማረፉ ከተጠመቅን በኋላ ሀብተ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሰጠን ሲያስረዳን ነው ። ማቴ 3፥16 ። በጥምቀት የተቀበልነው መንፈስ ቅዱስም ካልካድነው በቀር ምንም ኃጢአት ብንሠራ ንስሓ እስክንገባ ይጠብቀናል እንጅ አይለየንም ። ከሐዋርያት በኋላ የተነሱ ሐዋርያውያን አበው (ሊቃነ ዻዻሳት) ከተጠማቂው ህዝብ ብዛት አንጻር ለሁሉ ለማዳረስ እንዲቻልና ለሚቀጥለው ትውልድም የቤተ ክርስቲያን መመሪያ ሆኖ እንዲያገለግል በአንብሮተ ዕድ (እጅ በመጫን) ፋንታ የሚጠመቀው ምዕመን በቅብዓ ሜሮን አማካኝነት ሀብተ መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጥ ስለወሰኑ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያ ከጥምቀት በኋላ ለተጠማቂው ቅብዓተ ሜሮን በመቀባት መንፈስ ቅዱስን ታድላለች ።
የቃል ኪዳኑ ታቦት (ፅላት) ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ በመንበረ ክብሩ ላይ በመቀመጥ አገልግሎት እንዲሰጥ አስቀድሞ በዚህ በተቀደሰ ቅብዓ ሜሮን ተባርኮ መሰየም አለበት ። ተሰርቆ ወይም በሌላ ፤ ክብሩ በማይጠበቅበትና ተገቢ ባልሆነ ቦታ ቢቆይም ከተመለሰ በኋላ እንደገና መባረክ አለበት ።
ቤተ ክርስቲያን ከታነጸ በኋላ ፤ በውስጡ ሙሉ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከመስጠቱ በፊት በቅብዓተ ሜሮን መባረክ አለበት ። በቅብዓተ ሜሮን ካልተባረከ ቤተ ክርስቲያን ሊባል አይችልም ። ከተራ አዳራሽ የሚለየው በቅብዓተ ሜሮን ሲከብርና በውስጡም የቃል ኪዳኑ ታቦት ሲኖርበት ብቻ ነውና ።
3
ምሥጢረ ቁርባን
መግቢያ
ቁርባን ፤ ማለት ፣ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ አምኃ ፣ መስዋዕት ፣ መንፈሳዊ ነገር ሁሉ ማለት ሲሆን ፤ በዚህ ትምሕርታችን ግን ፤ ስለ ሐዲስ ኪዳን መስዋዕት (የክርስቶስ ሥጋና ደም) እንማራለን።
በብሉይ ኪዳን ለሐዲስ ኪዳን ቁርባን (መስዋዕት) ምሳሌዎች
የመልከ ጼዴቅ መስዋዕት ዘፍ 14 ፥ 18 ። ዕብ 5 ፥ 6 ። ዕብ 6 ፥ 1 ። ህብስቱ የሥጋው ፤ ወይኑ የደሙ ምሳሌ ፤ መልከ ጼዴቅ የክርስቶስ ፤ አብርሐም የምዕመናን ።
የእስራኤል ፋሲካ ። ዘፀ 12 ፥ 1 ። ሞት የዲያብሎስ ፤ እስራኤል የምዕመናን ፤ በጉ የክርስቶስ ምሳሌ ።
የእስራኤል መና ። ዘፀ 16 ፥ 13 ። መና የጌታችን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ፤ እስራኤል የምዕመናን ፤ ደመና የእመቤታችን
በብሉይ ኪዳን መስዋዕት ቁርባን ያቀረቡና በረከት ያገኙ አባቶች
አዳም አባታችን አዳም ባቀረበው መስዋዕት ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ሰው ሆኖ እንደሚያድነው ቃል ገባለት ። ዘፍ 3 ፥ 22 ። ገላ 4 ፥ 4 ።
ኖኅ ባቀረበው መስዋዕት ለኖኅና ለልጆቹ ምድርን ዳግም በመቅሰፍት እንደማያጠፋት በቀስተ ደመና ምልክት ቃል ገባላቸው ። ዘፍ 9 ፥ 1 ። ዘፍ 9 ፥ 8 ።
አብርሐም ዘፍ 18 ፥ 3 ። አባታችን አብርሐም ባቀረበው መስዋዕት በዘርህ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ የሚለውን የተስፋ ቃል ሰማ ፤ ያም ዘር የተባለው ለጊዜው ይስሐቅ ሲሆን፤ ፍጻሜው ግን ለጌታ ነበር ።
መልከ ጼዴቅ ዘፍ 14 ፥ 17 ። መዝ 109 ፥ 4 ። ዕብ 5 ፥ 6 ። በእግዚአብሔር ፊት ባቀረበው መስዋዕት ክህነቱ ለዘለዓለም ተብሎለት የክርስቶስ ምሳሌ ሆነ ። ዕብ 7 ፥ 1 ።
ዳዊት መዝ 131 ፥ 11 ። መስዋዕት ባቀረበበት ሠዓት ከአብራክህ የተገኘው ልጅህ በዙፋንህ ይነግሣል ተባለለት ፤ ይህም ለጊዜው የተነገረው ለሰሎሞን ሲሆን ፍጻሜው ለክርስቶስ ነበር ። መዝ 71 ፡1 ። ሌሎችም በእግዚአብሔር ፊት ንጹህ መስዋዕታ ቸውን እያቀረቡ በረከት ተቀብለዋል።
ምሥጢረ ቁርባን በሐዲስ ኪዳን
በብሉይ ኪዳን ዘመን ይቀርብ የነበረው የመስዋዕት ቁርባን ፤ ከበግ ፤ ከላምና ፤ ከተለያዩ እንስሳት ነበር ። በሐዲስ ኪዳን ግን እንስሳት በቤተ መቅደስ ውስጥ መስዋዕት (ቁርባን) ሆነው አይቀርቦም መስዋዕት ሁሉ በክስቶስ ሥጋና ደም ተጠቃሏል ።
ይህንም የአዲስ ኪዳን መስዋዕት የመሠረተው ራሱ ጌታችን ሲሆን ፤ በጸሎተ ሐሙስ ማታ አስራ ሁለቱ ሐዋርያት እንዳሉ በመጀመሪያ መስዋዕተ ኦሪትን ሰርቶ ካሳለፈ በኋላ ኅብስቱና ወይኑን ባርኮ “ነገ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬና የሚፈሰው ደሜ ይህ ነው ብሉ ጠጡ ብሎ ሰጣቸው” ። ማቴ 26 ፥ 26 ።
ዛሬ ካህኑ ኅብስቱን በጻህል ወይኑን በጽዋ አድርጎ ጸሎተ ቅዳሴውን እየጸለየ.. ሲባርከው እንደዚያ ጊዜው ኅብስቱ ተለውጦ ሥጋ መለኮት ወይኑም ተለውጦ ደመ መለኮት ይሆናል ። ይህንም ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም በምንቀበልበት ጊዜ ለእኛ ሲል የተቀበለውን መከራና ስቃይ እያሰብን ራሳችንን በንስሓ ከኃጢአት ንጹህ አድርገን ከንስሓ የቀረውን በደላችንን እንደሚደመስ ስልን ፤ ከበደል እንደሚያነጻንና የዘለዓለም ሕይወት እንደሚሰጠን አምነን መሆን አለበት ።
በ1ቆሮ 11 ፥ 23 “ይህንም ለመታሰቢያዬ አድርጉት ” የሚለው ቃል ሥጋውንና ደሙን በምንቀበልበት ጊዜ ስለሰው ልጆች ሲል በቀራንዮ አደባባይ የተበውን መከራና በልባችን ውስጥ የተሳለውን አምላካዊ ፍቅሩን እያስታወስን እንድንኖር ነው መታሰቢያ የሚለው ቃል የሚያመለክተው የማይረሳ ነገርን ነውና ። ገላ 3፥1
ጌታችን ይህን ምሥጢር ከማሳየቱ (ከመመስረቱ) በፊት በዮሐ 6 ፥ 25-8 ። “ሥጋዬን ካልበላችሁ ደሜንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም ሥጋዬን የበላ ደሜንም የጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ (ሕይወትን የሚሰጥ) ነው ” በማለት ስለምሥጢረ ቁርባን በስፋት አስተምሯል ።
የቅዱስ ቁርባን ጥቅም
ከዚህ ዓለም በሞት ብንለይም እንኳን በሰማያዊ መንግስት የማያልፈውን የዘለዓለም ሕይወት እናገኛለን ። ዮሐ 6 ፥ 54 ።
ለኃጢአታችን ስርየት (ፍጹም ድኅነት) እናገኛለን ። ማቴ 26 ፥ 26 ።
ከጌታችን ጋር ከቅዱሳንም ጋር ያለንን አንድነት እናረጋግጠጣለን ። 1 ቆሮ 10 ፥ 17 ።
ሥጋውን በስንዴ ደሙን በወይን ያደረገበት ምክንያት ትንቢቱንና ምሳሌውን ለመፈጸም ነው
ትንቢት
በልቤ ደስታ ጨመርሁ ከስንዴ ፍሬና ከወይን ፍሬ በዛ ። መዝ 4 ፥ 7 ። ይህም ቃል እውነተኛና ፍጹም የሆነው ዘለዓለማዊ መድኃኒት ቅዱስ ቁርባን በስንዴና በወይን እንደሚደረግ ያመለክታል ።
ምሳሌ
የክርስቶስ ምሳሌ፤ መልከ ጼዴቅ መስዋዕት የሚያቀርበው በስንዴና በወይን ስለነበረ ምሳሌውን ለመፈጸም ። ዘፍ 14 ፥ 17 ።
ሥጋውንና ደሙን በምግብ ያደረገበት ምክንያት
ምግብ ከሰውነት ጋር እንደሚዋሃድ ሥጋውንና ደሙን ስንቀበል በእውነት እንደሚዋሃደን ለማስረዳት።
ምግብ ለሥጋችን ኃይል እንደሚሆነን ሥጋውና ደሙም ለነፍሳችን መንፈሳዊ ኃይል ይሰጠናል።
አዳምና ሄዋን በምግብ የእግዚአብሔር ልጅነታቸውን እንዳስወሰዱ ፤ በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ልጅነታችንን ሊመልስልን ። ዘፍ 3 ፥ 1 ። ዮሐ 6 ፥ 49።
ቅዱስ ቁርባንን ፤ በበላችን ንስሓ ከገባን በኋላ ሁልጊዜ መቀበል ይገባናል ። የኃጢአታችን ስርየት የሚረጋገጠው በቅዱስ ቁርባን ነውና ። ማቴ 27 ፥ 27።
ምዕመናን በሕይወት እስካሉ ደረስ ወንድም ይሁን ሴት ፣ ታናሽም ይሁን ታላቅ ከቅዱስ ቁርባን መለየት የለባቸውም ይህ ምሥጢር በፆታ በዕድሜ የማይገደብ ለሁሉ የተሰጠ ነውና ። ዮሐ 6 ፥ 54 ። በሰራነው ስህተት ተጸጽተን ንስሓ ሳንገባ በድፍረት ሥጋውንና ደሙን መቀበል የለብንም ፤ ይህን የሚያደርጉ ሰዎች ዕዳ አለባቸው ። 1ቆሮ 11 ፥ 27 ። የምንቀበለው ቅዱስ ቁርባን ጌታችን በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ ከዋለ በኋላ ፤ ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን በራሱ ሥልጣን ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለይቷል ። ዮሐ 10 ፥ 18 ። ዮሐ 19 ፥ 30 ። በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ሄዶ በዚያ የነበሩ ነፍሳትን ወደ ገነት ከመለሰ በኋላ ሶስት መዓልትና ሶስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ከነበረው ሥጋ ጋር በፈቃዱ አዋህዶ ተነሳ ፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ግን(ሥጋውና ደሙ በተለያዩበት ወቅት) መለኮት ፣ ከነፍ ስም ከሥጋም ጋር አልተለየም ። 1ዼጥ ። ስለዚህ እኛ የምንቀበለው ሥጋና ደም ፤ ነፍስ የተለየችው መለኮት የተዋሃደው ነው ። 1ዼጥ 3 ፥ 18 ።
4
ምሥጢረ ንስሐ
መግቢያ
ንስሐ ፦ ነስሐ ተፀፀተ ካለው የተገኘ ሲሆን ፤ ንስሐ ማለት በሠሩት ኃጢአት መፀፀት ፣ ማዘን ፣ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ መወሰን ማለት ነው። ንስሐ ከዘለዓለማዊ ፍርድ የሚያድን ፤ ዘማዊውን እንደ ድንግል ፤ ሌባውን መጽዋች የሚያደርግ በፊት ከተሠራው ኃጢአት ንጹህ አድርጎ ፤ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የሚያደርግ ምሥጢር ነው ።
ከንስሐ በፊት
- መፀፀት
አንድ ክርስቲያን በድፍረትም ይሁን በስህተት “የሠራው በደል” መጻሕፍት በማንበብ ፣ ከመምህራን ተምሮ ፣ የስብከት ካሴት አዳምጦ ፤ ህሊናው ወቅሶት ፣ ወይም በሌላ በአንድ ምክንያት ስህተት መሆኑን ከተረዳ በኋላ ተፀፅቶ ከእግዚ አብሔር ለመታረቅ (በደሉን ለማስተስረይ) የሚያደርገው ጉዞ ንስሐ ይባላል ። በሠራው በደል ሳይፀፀት ፤ ለጊዜው ህሊናውን ስለረበሸው ብቻ ንስሐ የሚገባ ሰው ፤ ከስሐውን በኋላ ወደ ቀደመ ሕይወቱ ሊመለስ ይችላል ። ምክንያቱም ፡ ንስሐ የገባው ፡ በሠራው በደል ከልቡ ተፀፅቶ ሳይሆን ፤ በስሜት ተነሳስቶ ነውና ፤ - ኃጢአትን መጥላት
በበደላችን ከተፀፅትን በኋላ የሰራነውን በደል መጥላትና ወደፊትም መሥራት እንደሌለብን ራሳችንን ማሳመንና ከኃጢዓት መንገድ መራቅ ማለት ነው ። - ከንስሐ በኋላ ስላለው ሕይወት መወሰን
አንድ ምዕመን ንስሐ ከመግባቱ በፊት ለወደፊቱ የሚኖረውን ሕይወት አስቀ ድሞ መመርመርና መወሰን ይገባዋል የእግዚአብሔን ቃል ስንሰማ ለጊዜው ልባችን ሊነካ ፣ ምን እናድርግ ልንል እንችላለን ። የሐ ሥ 2 ፥ 37 ። ነገር ግን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ዓለሙን ወደመምሰል እንደማንመለስ አስቀድመን ራሳችንን መመርመር አለብን ። ብዙዎቹ በስሜት ወደ ክርስትና ከገቡ በኋላ ፤ በጊዜያዊ ነገር ተታለው በድንገት ከሃይማኖት መንገድ ወጥተዋልና ።
በንስሐ ጊዜ
አንድ ምዕመን ካለፈ በደሉ በንስሐ ታጥቦ በአዲስ ሕይወት ራሱን ለማስተካከልና ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር ከወሰነ በኋላ የንስሐ አባት ሊኖረው ይገባል ። ጌታችን “ካህናትን” ራሱን ወክለው መንጋውን እንዲጠብቁ “በምድር ያሰራችሁት በሰማይ የታሰረ በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሁን” (ማቴ 8 ፥ ዮሐ 21 ፥ 15 ። ማቴ 16 ፥ 19) በማለት መንጋውን እንዲጠብቁ ሾሟቸዋልና። አንድ ክርስቲያን በሕይወት ሲኖር ፤ የእግዚአብሔርን መንገድ የሚመራው ፤ ሲሳሳት ንስሐውን ተቀ ብሎ ቀኖና በመስጠት ከእግዚአብሔር የሚያስታርቀው የንስሐ አባት የግድ ሊኖረው ይገባል።
ንስሐ የሚገባው ምዕመን በካህኑ ፊት በሚቀርብበት ጊዜ የሚከተሉትን ማሟላት አለበት
- የሠራውን ስህተት በሙሉ ማስታወስ
ቀኖናው የሚሰጠው እንደ በደሉ ዓይነት ስለሆነ የሠራውን ማስታወስ አለበት ፤ በቃሉ የሚረሳው ከሆነም በጽሁፍ መመዝገብ ያስልጋል ። - ሳይቀንሱ (ሳይከፍሉ) በሙሉ መናገር
“ይህን ብናገር ሰው ምን ይለኛል ?” ብሎ ከባዱን (የሚያሳፍረውን) ነገር መደበቅ የለበትም። ሲሰራው ያላሳፈረውን ሲናገረው ሊያፍርበት አይገባም። አንድ ጊዜ ተናግሮ ከህሊናው ካላስወጣው ሁሌም ሲረብ ሸው ይኖራልና።“እናንተ ሸክማችሁ የከበደ ወደ እኔ ኑ ሸክማችሁን አራግፋለሁ” ማቴ 11 ፥ 28ተብሏልና በትክክል አስታውሶ መናዘዝና የኃጢአትን ሸክም ማራገፍ ይገባል። ስለ በደላችን በምንናዘዝበት ጊዜ ግን ፤ ከዕገሌ ጋር ፤ በዚህ ጊዜ ፤ በዚህ ቦታ ፤ ይህን አድርጌያለሁ እያልን ፤ ቦታውን ፤ ጊዜውን የሌላ ሰው ስም በዝርዝር እንድንናገር አንገደድም ፣ የሠራነውን በደል ብቻ “ጣዖት አምልኬያለሁ ፤ ሠርቄያለሁ ፤ አመንዝሬያለሁ” በማለት በጥቅሉ መናገር እንችላለን ። - ኑዛዜ (ራስን መክሰስ)
በራሳችን ድካም የሠራነውን በደል “ዕገሌ አሳስቶኝ” እያሉ ሌላውን ሰው ስለ እኛ ስህተት ተጠያቂ ማድረግ ሳይሆን ፣ አንደበታችንን ከሳሽ ህሊናችን ምስክር አድርገን በመጨከን ራሳችንን በእግዚአብሔር ፊት መክሰስ ነው ። አምላካችን የልባችንን መመለስ ፣ አይቶ የሰራነውን በደል ሁሉ እንዳልተሠራ አድርጎ ያነጻናል ። በደልን በንስሐ ይቅር ማለት የእግዚአብሔር የቸርነት ሥራ ነውና።
አንድ ምዕመን ንስሐ ከገባ በኋላ የሚከተሉትን በቅደም ተከተል ማድረግ አለበት?
- የተቀበለውን ቀኖና በትክክል መፈጸም
ቀኖና የግሪክ ቃል ሲሆን : መለኪያ ማለት ነው ። ካህኑ ለበደለው ምዕመን እንደ ሃይማኖቱ ጽናት ፣ እንደ አእምሮው ስፋት ፤ የሠራውን በደል መጥኖ ቀኖና ከሰጠው በኋላ እንደታዘዘው መፈጸም አለበት ። የነነዌ ሰዎች ፣ ት. ዮና 3 ፥1 ። ንጉሡ ህዝቅያስ ፣ ኢሳ 38 ፥ 1 ። ቅዱስ ጴጥሮስ ሉቃ 22 ፥ 54 ። እና ሌሎችም ይቅርታን ያገኙት ፤ በበደላቸው ተጸጽተው በማልቀሳቸውና ንስሃ በመግባታቸው ነው ። በንስሐ ወቅት ፡መሬት ላይ መተኛት ምግብ መቀነስ ፣ ከዓለማዊ ነገሮችና ለመንፈሳዊ ሕይወት ከማይመቹ ጓደኞች መራቅ ያስፈልጋል ። በንስሐ ጊዜ እንዳናደርግ ከታዘዝነው ነገር ራሳችንን በመግዛት መቆጠብ አለብን ፤ እግዚአብሔር በቸርነቱ ወደ ድኅነት ከጠራን በኋላ እንደገና ተመልሰን ወደተውነው ድካማችን መመለስ የለብንም። የጊዜውን ሳይሆን የመጨረሻውን ማሰብ አለብን ። 2 ጢሞ 4 ፥10 ። መዝ 6 ፥6 ። - በደላችን በንስሐ እንደሚሰረይልን ማመን
ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰው በደላችንን ለመደምሰስ ስለሆነ ከበደላችን ሊያነጻን የታመነ አምላክ ነው ። ከሠራነው ብዙ ኃጢአት አንጻር የሚሰጠን ቀኖና ትንሽ መስሎ ቢታየንም ። ማሰብ ያለብን የራሳችንን በደል ሳይሆን የእግዚአብሔርን ቸርነት ነው ። ከእኛ በደል የእግዚአብሔር የቸርነት ሥራው እጅግ ይበልጣልና የታዘዝነውን ፈጽመን የቀረውን እንደቸርነትህ ማለት ይገባል ። “የታዘዛችሁትን ባደረጋችሁ ጊዜ የማንጠቅም ባሪያዎች ነን በሉ” ተብለናልና ። ሉቃ 17 ፥ 10 ። - በሥጋውና በደሙ መታተም (መቁረብ)
አንድ የተራበ ሰው እጁን ስለታጠበ ብቻ አይጠግብም ። የግድ ምግብ መብላት አለበት ። ንስሐ ማለት መታጠብ ፣ ከእድፍ (ከኃጢአት) መንጻት ማለት ሲሆን ፤ ድኅነት የሚገኘው የዘለዓለም ሕይወት የሚሰጠውን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል ነው ። ዮሐ 6፥33 ። ብዙዎቹ መቁረብን እንደ ትርፍ ነገርና በዕድሜ የተገደበ (ለሽማግሌ ብቻ) አድርገው ስለሚቆጥሩት ለመቀበል ሲዘጋጁ አይታዩም ። ነገር ግን ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ቅዱስ ቁርባን የግድ ያስፈልገዋል ። ቀኖና የተቀበልንበት በደላችን የሚሰረየው ሥጋውን ስንበላ ፣ ደሙንም ስንጠጣ ነውና ። - ሁሌም ለንስሐ መዘጋጀት
ንስሐ ከገባንና ከቆርብን በኋላ እንደገና በኃጢአት ልንወድቅ እንችላለን። አምለካችን “ለምን ንስሐ አልገባህም እንጅ ለምን ኃጢአት ሠራህ? አይልምና” ሁለተኛ ስንበድል ሀፍረት ሳይሰማንና ከኃጢአት መላቀቅ ካልቻልሁ በየጊዜው የንስሐ አባቴን ከማስቸግር አርፌ ብቀመጥ ይሻለኛል በማለት ፡ ሁሉንም እርግፍ አድርገን እንድተወው ፡ ክፉ ሀሳብ በአምሯችን ሊፈታተነን ይችላል ።
ነገር ግን ከንስሐ በኋላ እንደ መላእክት በቅድስና ብቻ እንኖራለን ማለት ሳይሆን “ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃል ፤ ሰባት ጊዜ ይነሳል” ምሳ 24፥ 16 ። እንደተባለ ፡ አምላካችን ብንወድቅ ሊያነሳን ፤ ብንጠፋ ሊፈልገን ፤ ብንርቅ ሊያቀርበን ፤ በኃጢአት ብንረክስ ሊቀድሰን (እንደ ባዘቶ ሊያጠራን) የታመነ አምላክ ስለሆነ ተስፋ ሳንቆርጥ ፤ በኃጢአታችን ሳንደበቅ ፤ ዘወትር ለንስሓ መዘጋጀት አለብን። ኢሳ 1 ፥ 18 ።
5
ምሥጢረ ተክሊል
መግቢያ
ተክሊል ከለለ ፤ ጋረደ ። ካለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ነው። ተክሊል ማለት ፤ መከለል ፣ መወሰን ፣ መጋረድ ፣ መለየት ፣ ማለት ሲሆን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ለሚጋቡ ምዕማናን የሚፈጸምላቸው ሥርዓት ነው። እግዚአብሔር ወንድና ሴት አድርጎ ከፈጠራቸው በኋላ ምድርን ሙሏት ብሎ አዘዛቸው።(ዘፍ 1 ፥ 27) ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሴትና ወንድ በጋብቻ እየተሳሰሩ ልጆችን በመውለድ መባዛት ጀመሩ።
የጋብቻ ዓላማዎች
- ለመረዳዳት ፤ “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ አግባብ አይደለም የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት ። ዘፍ 2 ፥18 ።” ብሎ እግዚአብሔር እንደተናገረ ፤ ሰው በኑሮው ሁሉ እንዳይቸገር የውስጡን ሀሳብ የሚያካፍለው ፣ ችግሩን የሚጋራውና ራሱን የሚወክልለት የህይወት አጋሩን እየመረጠ ጋብቻ ይመሠርታል ።
- ለፈቃድ ፤ ሰው በባህርዩ ፍትወት (የተቃራኒ ጾታ ፍላጎት) አለበት ። ሰለሆነም በጋብቻ ተወስኖ እንዲኖርና ከፈተና እንዲጠበቅ ተፈቅዶለታል ። 1ቆሮ 7 ፥ 2-38 ። እንዲህ ዓይነቱ ጋብቻም መኝታው ንጹህ ነው ተብሏል ። ዕብ 13 ፥ 4 ።
- ለመባዛት ፤ ዛሬ በዓለማችን የምናየው የሕዝብ ቁጥር የተጀመረው በአንድ አዳምና በአንዲት ሄዋን ከተመሠረተ ህጋዊ ጋብቻ ነው ። ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት ብሎ የተናገረውና የፈቀደው እግዚአብሔር ስለሆነ እሰከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ በዚሁ መንገድ ልጆች ይወለዳሉ ። ዘፍ 1 ፥ 27 ።
ከጋብቻ በፊት
የተጋቢዎቹ ስምምነትአስቀድመው በጋብቻው ሁለቱም ተጋቢዎች መተወዋቅ መስማማትና መወሰን አለባ- ቸው ። ትዳርን ያህል ታላቅ ነገር በሌሎች ግፊትና ትእዛዝ መወሰን የለበትም ። እጮኛሞች ሲተዋወቁም በስህተት ውስጥ ወድቀው ሃይማኖታቸውን እንዳያስነቅፉ ግንኙነታቸው ከዓለማውያን ሰዎች ልዩ መሆኑን መዘንጋት የለባቸውም ። በመጠናናትም ጊዜ ማለፍ የለበትም ጊዜ በረዘመ ቁጥር ሃሳብ ይለዋወጣልና ።
የሃይማኖት አንድነት ፤ለጊዜው ቀላል መስሎ የሚታየው የሃይማኖት ጉዳይ ፣ በኋላ ለመፍታት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል ። በአንድ ሃይማኖት የሚያምኑና ሥርዓቱን ጠብቀው የተጋቡ ከሆኑ ግን እንደ አንድ ያስባሉ ሳይነጋገሩም በሀሳብ ይስማማሉ ፣ ይተሳሰባሉ….. ። በእርግጥ የሌላ እምነት ተከታይ የሆነውን አስተምሮ አሳምኖ ማግባት ይፈቀዳል ። ነገር ግን እሰብካለሁ ሲሉ መሰበክ እንዳይመጣ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ።
የአእምሮና የአካል ብስለት ፤ እንደ ቤተ ክርስቲያ ትምሕርት የጋብቻ ዕድሜ ፣ ሴት ከአሥራ አምስት ፤ ወንድ ከሃያ ዓመት ጀምሮ ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ሲሆን ፤ የአእምሮ ዝግጅት ማለትም ፤ ከሃይማኖት አንጻር ፡ ስለ ትዳር መማርና መረዳት ፣ ከትዳር በኋላ ስለሚኖረው ህይወት ግንዛቤ ማግኘት ፣ ከጋብቻ በኋላ ከትዳር ጓደኛው የሚቀርበው ሰው እንደሌለ ማወቅ ፣ ራስን ለትዳር ጓደኛ አሳልፎ ለመስጠት መወሰንና ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን በትዕግሥት ለማሳለፍ መዘጋጀት ናቸው ።
በጋብቻ ጊዜ
በውሳኔ መጽናት ፤ የሁለቱም ወገን ዘመዶችና ጓደኞች የራሳቸው ፍላጎት እንዲሆንላቸው በማሰብ ፤ ስለ ሠርጉ ፕሮግራም በማውጣት ከቤተ ክርስቲያን ውጭ እንዲደረግ ፣ ወይም ደግሞ በሁለቱም በቤተ ክርስቲያንም (በሥርዓተ ተክሊል እንዲፈጸም በመዘምራን እንዲታጀቡ) እንደገናም ፤ በዓለማዊ ሠርግ (በቬሎ እንዲወጡ ፣ በባንድ እንዲታጀቡ) በማዋከብ ግራ ሊያጋቡ ይችላሉ ። ነገር ግን የሚጋቡት አጃቢዎቹ ስላልሆኑ ፣ መወሰን ያለበት በሙሽሮቹ ነው ። ሙሽሮቹም በውሳኔያቸው መጽናት አለባቸው ። በውስጣቸው ያልተቆረጠ ዓለማዊ ፍላጎት ስላላቸውና ከእግዚአብሔር ቃል ይልቅ ለቤተሰቦቻቸው ምክርና ትእዛዝ ክብር በመስጠት ሠርጉ የተደበላለቀና ቅጥ ያጣ ፤ ብዙ ሰዎችንም የሚያሰናክል ሊሆን አይገባም ።
ጋብቻው በቅዱስ ቁርባን መሆን አለበት ፤ሥርዓተ ተክሊል የሚፈጸምላቸው የሥጋ ድንግልና ላላቸው ሲሆን ሌሎችም ክርስቲያኖች ጋብቻቸውን በቅዱስ ቁርባን ማድረግ ይችላሉ ። ክርስቲያናዊ ጋብቻ ያለ ቅዱስ ቁርባን አይደረግም ። አንዳንድ ሰዎች ፤ ለፎቶ ግራፍና ለቪዲዮ ሲሉ ብቻ ፣ ጋብቻቸውን በሥርዓተ ተክሊል ለማድረግ ያስባሉ ፣ ይህ ተገቢ ስላልሆነ አስቀድመው ስለ ጋብቻ ትምህርት በሚገባ መማርና ምርጫቸውን ከወዲሁ ማስተካከል ይገባቸዋል ።
ከጋብቻ በኋላ
ስምምነቱ ተጠብቆለት ሳይሆን በተፈጥሮ ህግ ነው ። እናትና አባቱን ይቀበላል እንጅ ለመቀበል ድርድር ውስጥ አይገባም ። ከእኛ በፊት የተደረጉ ነገሮችን በሙሉ አምነን እንድንቀበል ተፈጥሮ ያስገድደናል ። ትዳር ግን ተስማምቶ ወዶና ፈርሞ የሚገባበት ዘላቂ ሕይወት ስለሆነ ስምምነቱ እስከ ሕይወት ፍጻሜ የጸና ነው ። “ሰው እናትና አባቱን ይተዋል ወደ ሚስቱም ይጣበቃል ሁለቱም አንድ ይሆናሉ” ። ዘፍ 2 ፥ 24 ። ማቴ 19፥4 ። ባለው አምላካዊ ቃል መሠረት በትዳራቸው ውስጥ ማንም ሊገባ አይፈቀድለትም ።
ወላጆችም ቢሆኑ ልጆቻቸው ባይስማሙ ያስታርቃሉ ይመክራሉ እንጅ ለእነሱ ስላልተስማማቸውና ግላዊ ጥቅማቸው ስለቀረባቸው ብቻ ፍታት ፍቺው እያሉ የልጆቻቸውን ትዳር መበጥበጥ የለባቸውም የብዙዎች ትዳር የሚበተነው በቤተሰብ ጣልቃ ገብነት በመሆኑ ባለትዳሮች ይህን ጉዳይ አስቀድመው ሊረዱት ይገባል:: ባልና ሚስት አንድ ስለሆኑ በመካከላቸው ሁለትነት መታየት የለበትም ፤ ሰው ከቤተ ሰቡ ጋር የተዛመደው
ፍቺ የሚፈቅድባቸው ምክንያቶች
- ሞት
ከሁለቱ አንዳቸው በሞት ቢለዩ በሕይወት የቀረው ሌላ እንዲያገባ ተፈቅዶለታል ። ነገር ግን ጋብቻው በአንድ ሃይማኖት ከሚኖሩና በቅዱስ ቁርባን መሆን አለበት ። ሮሜ 7፥ 2 ። 1 ቆሮ 7 ፥ 39 ። - የጤና ጉድለት
በትዳር ለመኖር እስከማይችሉበት ድረስ በእንዳቸው ላይ የጤና(በጾታዊ አካላቸው ላይ) ችግር ካገጥማቸውና ለአብረው ለመኖር ካልተስማሙ መፋታት ይችላሉ ። ምክንያቱም ከጋብቻ መሠረታዊ ፍላጎቶች ከሆኑት ውስጥ አንዱ ስለተጓደለ ካልተስማሙ በቀር አብረው ለመኖር አይገደዱም ። - የሃይማኖት ልዩነት
አንዳቸው ከኦርቶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ወጥተው የሌላ እምነት ተከታይ ከሆኑና ተመክረው መመለስ ካልቻሉ በሃይማኖቱ የጸናው ትዳሩን መፍታት ይፈቀድለታል ። ነገር የተለየው ተመልሶ ካመነና ይቅርታ ከጠየቀ የትዳር ጓደኛውም ይቅርታውን ከተቀበለውና ከተስማማ በትዳራቸው መቀጠል ይችላሉ ። - ዝሙት
ከሁለቱ አንዳቸው በዝሙት ከወደቁ እና ከጥፋታቸውም መታረም ካልቻሉ ፤ ንጹሁ ሰው ትዳሩን መፍታት ይችላል ። ነገር ግን ወሬ በመስማትና በጥርጣሬ መሆን አለበት ። ማቴ 5 ፥ 32 ። የቤትን ገመና ለውጭ ማውራት ነገረ ሰሪ የሆኑ ሰዎችን ሊያስገባ ይችላልና መጠንቀቅ ያስፈልጋል ። የትዳር መሠረቱ በእውነት መግባባትና መተማመን ስለሆነ በሁኔታዎች መጠራጠርና መጨቃጨቅ አያስፈልግም ።
በዝሙት ኃጢአት የወደቀ የትዳር ጓደኛውም ከስህተቱ ተመልሶ ንስሐ ከገባና ይቅርታ ከጠየቀ ፤ እንደ በፊቱ በትዳራቸው መቀጠል ይችላሉ ። ባልና ሚስት በትዳራቸው በሚኖረው ማንኛውም ዓይነት ኑሮ በመመካከርና በመወያየት መወሰን አለባቸው ። ትዳር ፡ የሁለቱም የጋራ ሕይወት ስለሆነ ፤ መመሪያ አውጪና ተቀባይ መሆን የለባቸውም ። ገቢያቸውም ሆነ ወጪያቸው በጋራ መ ወሰን አለበት ። ትዳሩ እውነት የሚሆነው እነዚህ ሲሟሉ ነውና ።
የባለትዳሮችን አንድነት የበለጠ የሚያረጋግጡት የሚወልዷቸው ልጆች ናቸው ልጆች የሁለቱም እኩል ሀብቶች ስለሆኑ ያቀራርቧቸዋል ። ትዳራቸውንም ማክበር ያለባቸው የሚወዷቸው ልጆቻቸው እንዳይበታተ-ኑባቸው በማሰብ ጭምር መሆን አለበት ። በመካንነት ምክንያት መውለድ ያልቻሉት ባለትዳሮችም እግዚአብሔር ለእነሱ የወሰነላቸው የተሻለ መሆ ኑን በማሰብ ማመስገን ይገባቸዋል እንጅ በአምላክ ሥራ ገብተው ማማረር አይገባቸውም ። የተወለደውም ቢሆን ካልተባረከ ሊሞት ወይም መጥፎ ልጅ ሊሆን ይችላል ። እግዚአብሔር አውቆ ያደረገውን አምላካዊ ጥበብ ባለማወቅና ያሰቡት ስላልተሳ ካላቸው ብቻ ራሳቸውን የተረገመ አድርገው መቁጠር የለባቸውም እግዚአብሔር ያደረገው ሁሉ ለበጎ ነው ብሎ መቀበል ይገ ባል ። ገና ከማያውቋቸውና ካልተወለዱ ልጆች ይልቅ የሚወዱትና ከእግዚአብሔር አደራ የተቀበሉት የትዳር አጋራቸው እን ደሚበልጥባቸውም በማስተዋል ማሰብ ይገባቸዋል። (ዘፍ 30 ፥ 1)
6
ምሥጢረ ክህነት
መግቢያ
ካህን ፦ ተክህነ አገለገለ ። ካለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ፤ ካህን ማለት የእግዚአብሔር አገልጋይ ፤ የምዕመናን አባት ፤ ጠባቂ ፤ መጋቢ ማለት ነው ።
ምሥጢረ ክህነት በብሉይ ኪዳን
የክህነት አንዱ መገለጫው መስዋዕት ማቅረብ ሲሆን ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዚህ አገልግሎት የተመረጠውና ካህን ተብሎ የተጠራው መልከ ጼዴቅ ነው ። ዘፍ 14፥18 ። በኋላም እግዚአብሔር በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት በቤተ መቅደስ እግዚአብሔርን የሚያገለግል የሕዝቡን ኃጢአት እየተቀበለ ከእግዚአብሔር የሚያስታርቅ ካህን እንዲመርጥ ሙሴን ስላዘዘው ከመልከ ጼዴቅ በኋላ አሮን ተሾመ ።
ከአሮን እስከ ዮሐንስ መጥምቅ ደረስ ረጅሙን የብሉይ ኪዳን ዘመን ከአሮን ዘር ብቻ የሚወለዱት ቅብዓ ክህነት እየተቀቡ በካህንነት እያገለገሉ አልፈዋል ።
ነገር ግን በዘር ሐረግ ላይ የተመሠረተው ክህነት ለሐዲስ ኪዳኑ ክህነት ምሳሌ ስለነበረ ፍፁምና ዘላቂ አልነበረምና መስዋዕቱም ሆነ የአመራረጡ ሂደት በሌላ ተተካ ።
ዘላቂ ያልሆነበትና በሌላ የተተካበት ምክንያት
ክህነቱ በዘር ብቻ የተገደበ ስለነበረ በሐዲስ ኪዳን ህጉንና ሥርዓቱን አሟልቶ ለተገኘ ለማንኛውም ሕዝብ የተፈቀደ ሆነ ። ክርስቶስ የመጣው ለዓለም ሁሉ ነውና ።
መስዋዕታቸው ፍጹም ድኅነት የማያሰጥ በመሆኑ በክርስቶስ ሥጋና ደም ተተካ ። ዮሐ 6 ፥ 32 ።
አገልግሎቱ ለጊዜው ከሥጋ መቅሰፍት ከማዳን ያላለፈ ነበረ ፤ በሐዲስ ኪዳን ግን በምድርም በሰማይም ማሰር በሚችሉ ፣ በነፍስም በስጋም ላይ ሥልጣን ባላቸው ካህናት ተተካ ። ማቴ 18 ፥ 18 ።
ምሥጢረ ክህነት በሐዲስ ኪዳን
በብሉይ ኪዳን የመጨረሻው ካህን መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ሲሆን ፤ ከእሱ በኋላ የብሉይ ኪዳን ክህነት አልፏል ። ጌታችን ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ በዮሐንስ እጅ በመጠመቅ ፡ ካህኑ በሚገኝበት ቦታ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ሄደን በካህኑ እጅ መጠመቅ እንዳለብን አስተምሮናል ። ማቴ 3 ፥13 ።
ጌታችን ሲያስተምር ስለ ካህናት በብዙ ቦታ ተናግሯል ። ሂድና ራስህን ለካህን አሳይ ። ማቴ 8 ፥ 4 ። አንተ ብፁዕ ነህ ፡ የመንግስተ ሰማያትንም መክፈቻ እሰጥሃለሁ… ። ማቴ 16 ፥ 17 ። እውነት እላችኋለሁ በምድር ያሰራችሁት በሰማይ የታሰረ ፣ በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሆናል ። ማቴ 18 ፥ 18 ። ይህን የተናገረው በመዋዕለ ስብከቱ ሲሆን ከሙታን ከተነሳ በኋላም ለሐዋርያት አረጋግጦላቸዋል ። ሂዱና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው ። ማቴ 28 ፥ 19 ።..እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ ። ዮሐ 20 ፥ 22 ። በመጨረሻም ቅዱስ ዼጥሮስን “….ስምዖን ሆይ በጎቼን ጠብቅ ፤ (ለጊዜው አስራ ሁለቱን ሐዋርያት ፡ ለፍጻሜው ወላጆችን) ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ ፤ (ለጊዜው ሰብዓ አርድዕትን ፡ ለፍጻሜው ወጣቶችን) ፣ ግልገሎቼን ጠብቅ (ለጊዜው ሰላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስትን ፡ ለፍጻሜው ህጻናትን)” በማለት ሐዋርያትን ዸዸሳት ፣ ቅዱስ ዼጥሮስን የመጀመሪያ ሊቀ ዻዻሳት አድርጎ ሾመው ። ዮሐ 21 ፥ 15 ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን በሊቀ ዸዸስና በዸዸሳት በሚመራ መንፈሳዊ ጉባኤ (ቅዱስ ሲኖዶስ) አማካኝነት እየተመራች አገልግሎቷን ታካሂዳለች ።
የክህነት ደረጃዎች
- ሊቀ ዻሳሳት
ሊቃነ ዸሳሳት “ፓትርያርክ” እየተባለም ይጠራል ። በአንዲት ቤተ ክርስቲያን (በአንድ ሲኖዶስ) ላይ የበላይ ሆኖ የሚሾም የሁሉም አባት ነው ። የሐዋ ሥራ 20 ፥ 28 ። በሕዝብና በካህናት ከተመረጠ በኋላ በዻሳሳት ይሾማል ። ፍት ነገ 5 ። ረስጣ 2 ። ፓትርያርክ ያወገዘውን ዻዻስ አይፈታውም ። መንፈሳዊ ሥልጣኑ ከሁሉም በላይ ነውና። (ሲኖ 51) ፓትርያርክ በመላዋ ቤተ ክርስቲያን በጸሎት ጊዜ ስሙ ይጠራል ።
- ኤዺስ ቆዾስ
ዻዻስ በአንድ ሀገረ ስብከት አባት ሆኖ የሚሾም ነው ። ሲያገለግል በነበረበት አካባቢ ባሉ ምዕመናን ጥቆማና ድምጽ በርዕሰ ሊቃነ ዻሳሳቱና በሲኖዶስ ፈቃድ ይሾማል። (ፍት ነገ 5 : አብጥ 2) በአንድ ዻዻስ ብቻ አይሾምም። (ፍት ነገ 5 : ረስ 58 : ዲድ 34) ዻዻስ በሀገረ ስብከቱ በጸሎት ጊዜ ስሙ ይጠራል። (ፍት 5 : ክፍ 4) አዲስ ጽላት ፣ አዲስ ቤተ ክርስቲያን ፣ ይባርካል ። ለቄስ ለዲያቆን ሥልጣነ ክህነት ይሰጣል ። (1 ጢሞ 5 ፥ 2 : ፍት ነገ አን 5 ክፍ 4 )
- ቀሳውስት
ቅስና የሚቀበሉት በዲቁና ክህነት በማገልገል ላይ ያሉ ሲሆኑ ፤ በሁለት መንገድ ይሾማሉ ።
በምንኩስና የተወሰነ ያላገባ ጌታን እንዴት እንደሚያገለግል የጌታን ነገር ያስባል ( 1 ቆሮ 7 ፥ 32 ) በማለት ቅዱስ ዻውሎስ እንደተናገረ ፤ በምንኩስና ለመኖር የፈለገ አስቀድሞ ወደ ገዳም ሄዶ የምንኩስናን ሕይወት መማርና አባቶችን እያገለገለ በተግባር ማየት አለበት ። በገዳም የሚሰጠውን አገልግሎት ከፈጸመ በኋላ ፤ አበምኔቱ ሲፈቅድለት ሥርዓተ ገዳሙ በሚያዝዘው መሠረት መዓርገ ምንኩስና ይቀበላል ። (ይመነኩሳል)ከምንከስና በኋላ ለክህነት የሚያበቃውን ትምህርት ተምሮ በየደረጃው ያሉትን የሥልጣነ መዓርጋት። በድንግልና ከመነኮሰና በትም ሕርቱም ሆነ በግብረ ገብነቱ በቂ ሆኖ ከተገኘ እስከ መጨረሻው የቤተ ክርስቲያን መዓርግ “ጵጵስና” ሊደርስ ይችላል ።
በህግ የተወሰኑ ዲያቆናት በአንድ ህግ ከተወሰኑ ፤ በኋላ ለቅስና የሚያበቃ ትምህርትና ሥነ ምግባር ካላቸውና በሚያገለግ ሉበት አጥቢያ ሕዝብ ድምጽ ከተደገፉ ፤ ሊቀ ዻዻሱ ብቃታቸውን መዝኖ የቅስና መዓርግ ይሰጣቸዋል። (ፍገ ፡ 6)
ሰላሳ ዓመት ያልሆነው ቅስና አይሾምም ። ፍት ነገ ፡ 6 ። የቀሳውስት የአገልግሎት ድርሻ አስተምሮ ማጥመቅ ፤ ንስሐ መቀበልና መናዘዝ ፣ (ማሰርና መፍታት) ፤ ቀድሶ ማቁረብ ፤ ማስተማር…. ናቸው ።
ካህን የመጀመሪያ ሚስቱ ከሞተችበት ፤ መነኩሴም ምንኩስናውን ከተወው በኋላ የቅስና (የክህነት) ሥራ መሥራት አይፈ ቀድለትም ። ከማኅበረ ምዕመናን ግን አይለይም ።
ዲያቆናት
ዲያቆናት ካህናትን የሚራዱና የሚላላኩ ሲሆኑ ፤ በአገልግሎታቸው መሠረት የሚከተሉት ደረጃዎች አሏቸው
ዲያቆን
አስቀድሞ ሃይማኖቱን የተረዳ ፣ በምዕመናን ዘንድ በግብረ ገብነቱ የታወቀና የተመሰከረለት ፣ ለዲቁና አገልግሎት የሚያበቃውን ትምህርት ጠንቅቆ የተማረ ፤ ሆኖ ሲገኝ በአንብሮተ ዕድ (እጅ በመጫን) ይሾማል ። የተለየ ብቃትና ችሎታ ከሌለው በቀር ዕድሜው ከሃያ አምስት ዓመት በታች የሆነ ዲቁና አይሾምም ። ዲያቆን ከመጀመሪያ (ከህግ) ሚስቱ ከተፋታና ሌላ ካገባ ፣ ሃይማኖቱን ለውጦ በመናፍቃን ከተጠመቀ ፣ ከክህነቱ ይሻራል ። ፍት ነገ ፡ 7 ። ክፍል ፡ 5 ። ዲያቆናት መቅደስ ይገባሉ ፤ ነገር ግን መንበርና ታቦት ፣ (ከተለወጠ በኋላ) ሥጋውንና ደሙን በእጃቸው አይነኩም ። ዲያቆናት ለተልእኮ የሚፋጠኑ ፣ በትህትና የሚላላኩ ፣ በኑሯቸው ለሌላው አርአያ መሆን ይገባቸዋል ።
ንፍቀ ዲያቆን
የዲያቆን ረዳት ሲሆን ፤ መንፈሳዊ ሕይወቱ ፣ ግብረ ገብነቱና የሃይማኖቱ ጽናት በሚያገለግልበት አጥቢያ ካህናትና ምዕመናን የተመሠከረለት ። ፍት ነገ 8 ። ንፍቀ ዲያቆን በቃል ብቻ ይሾማል ፤ አንብሮተ ዕድ “እጅ በማጫን” አይደረግለትም ። ፍ ነ 8 ክፍ 2 ። የዲያቆን ረዳት እንደመሆኑ መጠን በሥራው ሁሉ ያግዘዋል እንጅ ንዋየ ቅድሳት አይነካም ። ፍት ነገ 8 ። ዶክ 45 ፣ 46 ። ጥፋት ሠርቶ ከተገኘ ከክህነቱ ይሻራል ። ፍት ነገ ፡ 8 ፡ ክፍል ፡ 4 ።
አናጉንስጢስ
አገልግሎቱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጻሕፍት ማንበብ ሲሆን ፤ ትምህርቱና በግብረ ገብነቱ ከታየ በኋላ ተመ ርጦ ይሾማል ። ፍት ነገ 8 ክፍል1 ። አናጉንስጢስ አንብሮተ ዕድ አይደረግለትም በቃል ብቻ ይሾማል ። ፍት ነገ 8 ፡ ክፍ ፡ 2 ። በአገልግሎት ጊዜ ዲያቆናት በቅዳሴ ሠዓት የሚለብሱትን ልብሰ ተክህኖ አይለብስም ። ፍት ነገ 8 ፡ ክፍ 3 ። አናጉንስጢስ ጥፋት ከተገኘበት ከሥራ ታግዶ ከዓመት በኋላ ይመለሳል ። ከጥፋቱ ካልታረመ ከአገልግሎቱ ይሻራል ። ፍት 8 ክፍል 4 ። ሚስቱ ከሞተችበት ሌላ አግብቶ ማገልገል ይችላል ። ፍት ፡ 4 ፡ ክ ፡ 5 ።
መዘምራን
በቡራኬ ይሾማሉ ። ፍ ነገ ፡ 8 ክፍ ፡ 2 ። ከመዝሙረ ዳዊት ፣ በሀገራችን የቅዱስ ያሬድን ዝማሬም ይዘምራሉ ። በሚዘምሩበት ጊዜ ልብሰ ተክህኖ አይለብሱም ። ፍት ገነ ፡ 8 ክፍ ፡ 3 ። መዘምራን ሚስታቸው ከሞተችባቸው ሌላ ማግባት ይችላሉ ። ፍት ነገ ፡ 8 ክ ፡ 5 ። በሀገራችን መዘምራን ማለት የማኅሌት ትምህርት የተማሩትን ሲሆን ፤ እነዚህም ሥልጣነ ክህነት (ዲቁና ቅስና ፣ ከዚያም በላይ) ካላቸው በሁለቱም (በማኅሌትም በክህነታቸውም) ማገልገል ይችላሉ ። የሰንበት ት“ምህርት መንፈሳውያን ወጣቶችም መዘምራን ይባላሉ ።
አጻዌ ኆኅት
በቃል ብቻ ይሾማል አገልግሎቱ በር መክፈትና መዝጋት ሲሆን ልብሰ ተክህኖ አይለብስም ። ፍት ነገ 8 ፡ ክፍ ፡ 3 ። ሚስቱ ከሞተችበት ሌላ አግብቶ ማገልገል ይችላል ። ፍት ነገ ፡ 8 ፡ ክፍ ፡ 3 ።
ሴቶች ዲያቆናውያት
በትዳር ተወስነው የኖሩ ፣ ልጆቻቸውን በሥርዓት ያሳደጉ ፣ በቅዱስ ቁርባን የተወሰኑ ፣ ለአገልግሎት የ ሚፋጠኑ ፣ 8 ዓመት የሆናቸው ፤ ዲያቆዊት ሆነው በቃል ይሾማሉ ። 1 ጢሞ 5 ፥ 9 ። ፍት ፡ ነ 8 ፡1 ። ዲድ 17 ።
- አገልግሎታቸው
ከካህናቱ ወደ ሴቶች ይላላካሉ ፤ ሴቶች ክርስትና ሲነሱ ፤ ካህኑ እጃቸውን ይዞ ከአንገተችው በታች ቅብዓ ሜሮን ይቀባሉ።
አይባርኩም ፤ ቄስና ዲያቆን የሚሠራውን የክህነት ሥራ አይሠሩም በሴቶች በር ቆመው ይቆጣጠራሉ ።
እንደ ዲያቆኑ ተንሥኡ ጸልዩ አይሉም ቅስና አይሾሙም ጉባዔ በጸሎት አይከፍቱም ። (ፍነ 8 ክፍ 1)
እነዚህም ፤ ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ ከሌላው ምዕመን ተለይተው እነሱ ወደ ቤተክርስቲያን ስለቀረቡ ፤ ምዕመናን በሥጋ ድካም ቢሳሳቱ ፤ ከሚያገለግሉት ጓደኞቻቸው መካከልም የተሳሳተ ወንድማቸው ቢኖር ሊመክሩት ፤ ሊያጽናኑት ይገባል እንጅ ፤ የራሳቸውን ጽድቅ የወንድማቸውን ስህተት እያወሩ ፤ ለሚድኑት መሰናክል መሆን የለባቸውም። (ሉቃ 18 ፥ 9)
7
ምሥጢረ ቀንዲል
መግቢያ
ቀንዲል (ቅብዓ ቅዱስ) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘይት እተተባለ ይጠራል። የሚጋጀውም ከንጹህ ወይራ ዘይት ሲሆን ፤ ህሙማነ ሥጋና ህሙማነ ነፍስ እየተቀቡ የሚፈወሱበት የተቀደሰ ቅባት ነው ።
በዚህም የተቀደሰ ቅባት በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩ ሰዎች በሚታመሙ ጊዜ ፡ እየተቀቡ ይፈወሱበት ነበር ። ኢሳ 1 ፥ 6 ። ሉቃ 10 ፥ 34 ።
በሐዲስ ኪዳንም ሐዋርያት ህሙማነ ሥጋንና ህሙማነ ነፍስን ቅብዓ ቅዱስ እየቀቡ ከነበረባቸው ደዌ ፈውሰዋቸዋል ። ማር 6 ፥ 13 ። በቀጣይም ፡ ምዕመናን በሚታመሙበት ጊዜ ፤ ካህናት እንዲጸልዩላቸውና ቅብዓ ቅዱስ ቀብተው እንዲፈውሷቸው ታዝዘዋል። (ያዕ 5 ፥ 14)
የቅብዓ ቅዱስ ጥቅም
ቅብዓ ቅዱስ በማንኛውም ዓይነት በሽታ በተለይ በቁስል ለተመቱና ጆሯቸው ለታመመባቸው ሰዎች ፤ እንዲሁም ደዌ ነፍስ ላደረባቸውና ረድኤተ እግዚአብሔር አጋዥ እንዲሆናቸው ፣ ከኃጢአታቸውም እንዲነጹ የፈለጉ ምዕመናን ፤ ካህኑ ጸሎተ ቀንዲል ጸልዮ በሚቀባቸው ጊዜ ከነበረባቸው የሥጋና በሽታና የነፍስ ደዌ (ኃጢአት) ይፈወሳሉ ። ነገር ግን በሚቀቡበት ጊዜ እግዚአብሔር በዚህ የተቀደሰ (ዘይት) ቅብዓ ቅዱስ ላይ አድሮ ካደረባቸው ደዌ ፡እንደሚያድናቸው በፍጹም ልባቸው ማመን አለባቸው ።
ቅብዓ ቅዱስ የሚቀቡ ፤ አምነው የተጠመቁ ክርስቲያኖች ሲሆኑ ፤ ከመቀበቀታቸው በፊት ንስሐ መግባትና ራሳቸውን መቀደስ አለባቸው ። ሥርዓቱ የሚፈጸመው በካህናት ሲሆን ፤ በመጀመሪያ ጸሎቱ ቤተ ክርስቲያን ወይም ታማሚው በተኛበት ቦታ ዙሪያ ፡ ያም ባይሆን በካህኑ ጸሎት ቤት ከተጸለየበት በኋላ የታመመው (የቆሰለው) ቦታ ላይ ይቀባል ።