መግቢያ

አምድ ፤ ማለት ምሰሶ ማለት ሲሆን አእማድ ማለት ምሰሶዎች ማለት ነው ። ቤት በአምድ (በኮለም) እንደሚፀና ፤ ሃይማኖትም በነዚህ ምሥጢራት ተጠቃሎ ይገለጻል ፤ ምዕመናንም እነዚህን ምሥጢራት በመማር ፀንተው ይኖራሉ።
ምሥጢር ፤ ማለት ለተወሰነ ጊዜ በተወሰኑ ሰዎች ብቻ ተጠብቆ የሚቆይ ሲሆን ፤ በዚህ ትምህርታችን ግን በሚታዩ ምሳሌዎች የማይታየውን የሃይማኖት ምሥጢር መረዳት ፤ በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ፀጋ ማግኘት ማለት ነው።
አምስት ፤ ቁጥራቸው አምስት ብቻ ሆኖ የተወሰነው ፤ በ 1 ሳሙ 17 ፥ 40። እና በ1 ቆሮ 14 ፥ 19 ። ባለው ቃል መሠረት ሲሆን ፤ አምስት መሆናቸውና የተደረጉባቸው ድንቅ ሥራዎች የአምስቱ አእማደ ምሥጢር ምሳሌነታቸውን ያስረዳል።

1

ምስጢረ ሥላሴ

መግቢያ

ሠለሰ ሶስት አደረገ ፤ ካለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ፤ ሥላሴ ማለት ሶስትነት ማለት ነው ። በዚህ ትምህርት የአምላክን አንድነት ሶስትነት እንማራለን ።

የምሥጢረ ሥላሴን ትምህርት በምንማርበት ጊዜ ከሂሳብ ቀመር ህግ አስተሳሰብ ውጭ ሆነን ነው ። ምክንያቱም መንፈሳዊዉ ሥጋዊዉን ጥበብ (ፍልስፍና) ይመረምረዋል እንጅ መንፈሳዊ ጥበብና ምሥጢር በዓለማዊ ዕውቀት ምርምር ሊደረስበት አይቻልምና ። የሃይማኖት ነገር ቁሳዊ ሳይሆን መንፈሳዊና በሃይማኖት ሆኖ በመንፈሳዊነት የሚታወቅና የሚታመን ነው ።

የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት በብሉይ ኪዳን

“ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር አለ” ዘፍ 1 ፥ 26 ። ። ከዚህ ቃል በፊት እግዚአብሔርን የሚመስል ፍጡር መኖሩን የሚገልጽ ባለመኖሩ “በመልካችን…” የሚለው አምላክ ከአንድ በላይ የሆነ የራሱ መልክ እንዳለው ያስረዳል። እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር ማንም ረዳት እንዳላስፈለገው በኢሳ ፡ 40 ፥ 12 ። ላይ ተጽፎ እናገኛለን ። በመሆኑም “በመልካችን..”የሚለው ሶስትነቱን (ከአንድ በላይ መሆኑን) ፤ “አለ” የሚለው ደግሞ አንድነቱን ይገልጽልናል ።

“አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” ዘፍ 3 ፥ 22 ። እግዚአብሔር በአካልና በስምና በግብር ሶስትነት ባይኖረው ኖሮ “እንደ እኔ ሆነ” በማለት ይናገር ነበር ። “ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” የሚለው ግን ብዙ ቁጥርን አመላካች በመሆኑ እግዚአብሔር አንድ ብቻ እንዳልሆነ ያስረዳናል ።

ዘፍ 11፥7 ። “ኑ እንውረድና ቋንቋቸውን እንደባልቀው አለ” ይህ ቃል አንዱ ሌሎቹን ኑ እንደሚል እንረዳለን ። በዚህም እግዚአብሔር ለአምላክነት ሥራው የማንንም እርዳታ እንደማይፈልግ የሚታወቅ ሲሆን በውስጡ ከሁለት በላይ እንደሆነ አንዱ ሌሎቹን “ኑ” በማለቱ ያስረዳል ።

ዘፍ 18 ፥ 1 ። እግዚአብሔር በመምሬ ዛፍ ስር ለአብርሐም ተገለጠለት ። አብርሐምም ዓይኑን አነሳና ሶስት ሰዎችን አየ የሚለው እግዚአብሔር በሶስትነቱ በሰዎች አምሳል ለአብርሐም መገለጡን በቁጥር ሶሰት ብሎ ያስረዳል ። ሀሳቡን ግልጽ ለማድረግ እግዚአብሔር ከሶስት ሰዎች ጋር ወይም ከሁለት መላእክት ጋር ተገለጠለት አይልም ። መላእክትም ሆኑ ሰዎች በዚህ ሥም አይጠሩም ኢሳ 42 ፥ 8 ። እስከዚህ ድረስ ብዛትን ብቻ ሲያመልክት የነበረው በዚህ ላይ ሶስት ብሎ ለይቶ ስለተናገረ እግዚአብሔር ሶስትነት ያለው መሆኑን በግልጽ ያስረዳል ።

የእግዚአብሔር ሶስትነት

እግዚአብሔር ፤ በስም ፤ በግብር ፤ በአካል ፤ ሶስት ነው ።

የስም ሶስትነት

አብ ፡ ወልድ ፡ መንፈስ ቅዱስ፡በመባል ነው ። “ሂዱና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው” ማቴ ፳፰ ፥ ፲፱ ። የአብ ፍቅር ፤ የወልድ ፀጋ ፤ የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ፤ የሚለው ቃል ሶስትነቱን በግልጽ ያስረዳል ። 2ቆሮ 13 ፥ 14 ።

ስሙ (የወልድ) ፤ የአባቱ ስም ፤ የመንፈስ ቅዱስ ስም ፤ የተጻፈባቸው ። ራዕ 14 ፥ 1 ። ከላይ የተገለጹት የእግዚአብሔርን የስም ሶስትነት ያስረዳሉ ።

አብ ፤ በራሱ ሥም አብ ይባላል እንጅ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አይባልም ። ሶስቱም በየስማቸው ይጠራሉ ። ሃይ አበው ምዕ 11. ክፍል 1 ፡ 7 ።

“ሥላሴ” ማለት ሶስትነት ማለት ሲሆን ፤ የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ የሶስትነት ጥቅል ስም ነው ። “ሥላሴ” በምን ልበት ጊዜ አብ ፤ ወልድ ፤ መንፈስ ቅዱስ ፤ ማለታችን ነው ።

የግብር ሶስትነት

ግብር ሥራ ማለት ሲሆን ፤ በዚህትምህርት የእግዚአብሔርን የግብር ሶስትነት አብ አባት ፤ ወልድ ልጅ ፤ መንፈስ ቅዱስ ሰራጺ መሆናቸውን እናያለን ።

አብ ማለት አባት (ወልድን የወለደ) ። ማቴ 3፥17 ። አስራጺ ፡ መንፈስ ቅዱስን ያሰረጸ ። ዮሐ 15፥26 ።

ወልድ ፤ ተወላዲ (ከአብ የተወለደ) ። ሉቃ 1 ፥ 35 ። መንፈስ ቅዱስ ማለት ፤ ሰራጺ (ከአብ የሰረጸ) ። ዮሐ ፲፭ ፥ 26 ። ማለት ነው ።

አብ አባት ፣ ወልድ ልጅ ፣ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ (ሕይወት) ፣ በማለቱ ። የግብር ሶስነቱ የስሙን ሶስትነት ይገልጻል ። ይህ ማለት ግን አብ አባትና አስገኝ ፣ ስለተባለ ከአብና ከወልድ አይቀድምም አይበልጥም ፤ ወልድም ከአብ አያንስም ፤ ከመ ንፈስ ቅዱስ አያንስም ፤ መንፈስ ቅዱስም ከአብ ከወልድ አያንስም ። ሁሉም እኩል በአንድነትና በሶስትነት ይመሰገናሉ ።

የአካል ሶስትነት

ለአብ ፣ ለወልድ ፣ ለመንፈሰ ቅዱስ ለየራሳቸው ፍፁም ገጽ ፣ ፍፁም መልክ ፣ ፍፁም አካል፣ አላቸው ።

ገጽፊት ማለት ሲሆን፣ ከአንገታችን በላይ የሚታዩት የሰውነት ክፍሎቻችንን ዓይን ፣ ጆሮ…. የመሳሰሉትን ያጠቃልላል ።

መልክበእያንዳንዳቸው የሰውነታችን ክፍሎች (እግር ፣ እጅ ፣ ራስ ፣ ፀጉር ፣ ዓይን ፣ ጆሮ…..) ተብለው ሲቆጠሩ ነው ።

አካል በአጠቃላይ ሙሉው የሰውነታችን ክፍል ነው ። የፍጡራን አካል የሚታይ ፣ የሚዳሰስ ፣ የሚመጠን ፤ የሚወሰን ፣ ሲሆን የሥላሴ አካል ግን ፤ የማይታይ ፣ በእጅ የማይዳሰስ ፣ በቦታ የማይወሰን ፣ በሁሉም ሙሉ ነው ። መዝ 138 ፥ 7 ።

የእግዚአብሔር የአካል ሶስትነት ። በማቴ 3 ፥16 ። እንደተገለጠው አብ በደመና ፣ ወልድ በለበሰው ሥጋ ፣ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በመሆን በግልጽ ታይቷል ። በሌላም በኩል ለአብርሐም በሶስት ሰዎች አምሳል የተገለጠለት ፣ በአካል ሶስት መሆኑን ሲያስረዳው ነው ። የሥላሴ ሶስትነት ከሰዎች የሂሳብ ቀመር ልዩ ስለሆነ (ቅድስት ሥላሴ) ልዩ ሶስትነት ይባላል ። በሂሳብ ህግ አንድ ሲሆን ሶስት…. የሚሆን ነገር የለምና ። የየራሳቸው የሶስትነት ፣ ሥም ፣ ግብር ፣ አካል ፣ አላቸው ።

የእግዚአብሔር አንድነት

የእግዚአብሔር ሶስትነት በሶስት ነገሮች በስም ፣በግብር፣በአካል፣ ብቻ ሲሆን በሌላው ሁሉ ለምሳሌ በባህርይ በህልውና ዮሐ 14 ፥ 8 ። በፈቃድ ፣ በሥልጣን ፣ በመፍጠር… ፣ አንድ ነው ። ለአብ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ በተለያየሥራና ደረጃ ተጽፎ ብናገኝም የስማቸውን የግብራቸውንና የአካላቸውን ሶስትነት ለመግለጽ እንጅ በአንዱ ሥራ ሁሉም አሉበት ። ዓለምን ፈጥሮ እየገዛ ያለ ፣ ሰው ሆኖ ዓለምን ያዳነ ፣ አምላክ አንድ ብቻ ነው ። ኤፌ 4 ፥ 5 ።

ኩነት (ከዊን)

ኩነት ወይም ከዊን ማለት ሁኔታ ወይም መሆን ማለት ሲሆን ፣ ይህም በሰው ነፍስ ምሳሌ ይገለጻል ። ነፍስ አንዲት ስትሆን ሶስት ባህርያት (ኩነታት) አሏት ፤ እነሱም ፤ ልብ (ማሰብ) ፤ ቃል (መናገር) ፤ እስትንፋስ (ሕይወት) ናቸው ። ከሶስቱ ባህር ያት አንዱ ከተጓደለ ነፍስ የሚለውን ስም ልታገኝ አትችልም ።

የእግዚአብሔር ሶስትነት በሰው ነፍስ ምሳሌ ሆኖ ቀርቧል ። ይኸውም አብ በልብ (ማሰብ) ፣ ወልድ በቃል (መናገር) ፣ መን ፈስ ቅዱስ በእስትፋስ (ሕይወት) ሲሆን አብ ለራሱ ልብ ሆኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ልባቸው ነው ። ወልድም ለራሱ ቃል ሆኖ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው ። መንፈስ ቅዱስም ለራሱ ሕይወት ሆኖ ለአብና ለወልድ ሕይወታቸው ነው ። በእግዚአብሔርነቱ ፤ ልብ ፣ ቃል ፣ ሕይወት አለ ። ነፍስ ሶስት ባህርያት ቢኖሯትም አንድ እንደምትባል እግዚአብሔርም ሶስት ስም፤ ሶስት ግብር ፤ ሶስት አካል ፤ ቢኖረውም አንድ አምላክ እንጅ ሶስት አማልክት አይባልም ። ዘዳ 6 ፥፬ ። ሚል 2 ፥ 10 ።

የእግዚአብሔርን አንድነትና ሶስትነት ለማስረዳት የቀረቡ ምሳሌዎች

ፀሀይ

አካል (መጠን) ብርሃን ሙቀት አላት ። በአካሏ አብ ፣ በብርሃኗ ወልድ ፣ በሙቀቷ መንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሆነው ቀርበዋል ። ፀሀይ ሶስት ሁኔታዎች ሲኖሯት አንድ እንደሆነች እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ሶስት ፤ ሶስት ሲሆን አንድ አምላክ ነው ።

ውሃ

ይዘት(ስፋት) ፣ እርጥበት ፣ ቅዝቃዜ አለው ። በይዘቱ (በስፋቱ) አብ ፣ በእርጥበቱ ወልድ ፣ በቅዝቃዜው መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ ። ውሃ አንድ እንደሆነ እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ሶስት ፤ ሶስት ሲሆን አንድ አምላክ ነው ። ሌሎቹም በምሳሌነት የሚቀርቡ ፍጥረታት አሉ ። ነገር ግን በምሳሌነታቸው ለማስተማር እንጅ የአምላክን ባህርይ የፍጡር ባህርይ ሊያስረዳ አይችልም ።

 

2

ምሥጢረ ሥጋዌ

መግቢያ

ሥጋዌ : ተሰገወ ሰው ሆነ ካለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን : ምሥጢረ ሥጋዌ ማለት ሰው የመሆን ምሥጢር ማለት ነው::

አምላክ ለምን ሰው ሆነ?

  1. አዳምን ከበደል ሊያነጻው

አዳም የሰይጣንን ምክር በመስማት እግዚብአሔር አትብላ ያለውን ዕፀ በለስ በልቶ ትእዛዙን በማፍረሱ ከፈጣሪው በተጣላ ጊዜ የሞት ፍርድ (ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ) ተፈረደበት ። ዘፍ 3፥1 ። ለጥፋቱ ምክንያት የነበሩት ዕባብና ሄዋንም እንደ ጥፋታቸው መጠን ተረግመዋል ። ዘፍ 3፥14 ።

አዳምም ጥፋቱን አምኖ ንስሓ ስለገባ አምላክ ሰው ሆኖ እንደሚያድነው ቃል ገባለት ። ዘፍ 3 ፥ 22 ። ቃል ኪዳኑም “አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” የሚለው ሲሆን እግዚአብሔር ወልድበተለየ ስሙ ፣ በተለየ ግብሩ ፣ በተለየ አካሉ ፣ ሰው ሆኖ እንደሚ ያድነው ቃል መግባቱን ይገልጻል ።

ለአዳም በገባው ቃሉ መሰረት ጊዜው ሲደርስ ከተፈረደበት ፍርድ ነፃ ሊያወጣው (ሊያድነው) ሰው ሆነ ። ገላ 4 ፥ 4 ። ጊዜው ማለት አምስት ሺህ አምስት መቶ (አምስት ቀን ተኩል ሲፈጸም) ማለት ነው ። መዝ 84 ፥ 4 ።

  1. የሥጋን በደል ለመካስ

አዳም ፤ ዕፀ በለስን በበላህበት ቀን ሞትን ትሞታለህ (ዘፍ 2፥ 17) ያለውን አምላካዊ ቃል ተላልፎ በለስን በመብላቱ የሞት ፍርድ ከተፈረደበት በኋላ ንስሃ በመግባቱ አምላክ ትሞታለህ ያለው ፍርዱ ሳይሻር ይቅር ይለው ዘንድ ወደደ ። በመሆ ኑም በመለኮታዊ ባህርዩ ሞት ስለማይስማማው የሚሞት ሥጋን ለብሶ (ሰው ሆኖ) ቅጣቱን ሊቀበልለት ። ኢሳ 53፥1 ። የእግዚአብሔር ቸርነቱ የባህርዩ ስለሆነ ሞቱን ሞቶ ፍርዱን በመፈጸም ይቅር ብሎ ቸርነቱን በማድረግ ፍርዱንም ይቅር ባይነቱንም በአንድ ጊዜ ሊገልጽ ፈቃዱ ስለሆነ

  1. ፍቅሩን ለመግለጽ

እኛ ሰዎች ምንም ያህል ሰውን ብንወድ ቁሳዊ ነገር ልንሰጥ እንችላን ። እርሱንም ቢሆን ጥቅማችንን (ትርፋችንን)አይተን ነው ። አምላካችን ግን ከእኛ ምንም ላያገኝ ባህርዩን ዝቅ አድርጎ ደካማ ባህርያችችንን በመዋሃድ በአዳም የተፈረደውን ፍርድ እርሱ ተቀብሎ በማዳን እውነተኛ ፍቅሩን ሊገልጽልን ስለወደደ ። ዮሐ 15 ፥ 13 ። ዮሐ 10 ፥ ፲፩ ። ኢሳ 40 ፥ 11 ።

 

እንዴት ሰው ሆነ ?

  1. የሚወለድበት ጊዜው ከመድረሱ አስቀድሞ በነቢያት አድሮ ምሳሌ አመስሏል ትንቢት አናግሯል ።

    ምሳሌ፡

    የመልከ ጼዴቅ ክህነት። መልከ ጼዴቅ የጌታ ፤ አብርሐም የምዕመናን ። ዘፍ 14 ፥ 18 ። ዕብ 7፥ 1 ።

    የይስሐቅ ቤዛ ሆኖ የተሰዋው በግ። ዘፍ 22 ፥18 ። ይስሐቅ የአዳም ፣ በግ የጌታ ምሳሌ ። ዮሐ 1፥29 ።

    የእሥራኤል መና ። ዘፀ 16 ፥ 13 ። እሥራኤል የአዳም ፣ መና የጌታ ምሳሌ ። ዮሐ 6 ፥ 32 ። ግብፅ የሲኦል ፤ ከነዓን የመንግስተ ሰማያት ፤ ባህረ ኤርትራ የኃጢአት ፤ የሙሴ በትር የመስቀል ፤ ምሳሌ ሲሆን ሌሎችም በርካታ ምሳሌዎች አሉ።

    ትንቢት፡

    እግዚአብሔር በሴም ቤት ይደር ። ዘፍ 9፥26 ። እግዚአብሔር የተባለው ወልድ ቤት እመቤታችን ።

    በዘርህ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ። ዘፍ 20፥17 ። ዘር የተባለ ጌታ አሕዛብ የተባሉ ሰዎች ። ገላ 3 ፥16 ።

    ኮከብ ከያዕቆብ ይወጣል ። ዘኁ 24፥17 ። ኮከብ የጌታ ፤ ያዕቆብ የሰው ልጅ ምሳሌ ። ማቴ 2 ፥ 7 ።

  2. ብስራተ መልአክን በተቀበለችበት ሰዓት

    መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ባበሰራት ጊዜ እንደ ቃልህ ይደረግልኝ ብላ ስትቀበል ቃሏን ምክንያት አድርጎ መለኮታዊ ባህርዩን ከሰው ደካማ ባህርይ ጋር በማዋሀድና ከሁለት አካል አንድ አካል ፤ ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ በመሆን ፍፁም ሰው ፤ ፍፁም አምላክ ሆነ ። ይህም ማለት መለኮታዊ ባህርዩን ከሰው ባህርይ ጋር አንድ አድርጎ(አዋህዶ) ሰውና አምላክ (ፍጹም ሰው ፤ ፍጹም አምላክ) ሆነ ። ሉቃ 1 ፥ 30 ። ማቴ 1 ፥ 23 ። ዮሐ 1 ፥ 14 ።

  3. ሲዋሃድም

    እንበለ ውላጤ፤ ያለ መለወጥ።

    እንደ ሎጥ ሚስት ። ዘፍ 19 ፥ 26 ። እንደ ቃና ውሃ ። ዮሐ ፡ 2 ፥ 1 ። ያይደለ ።

    እንበለ ቱሳሄ ፤ ያለመቀላቀል።

    እንደ ማርና ውሃ ሳይቀላቀሉ ፤ በመጠባበቅ ቃልም ሥጋም ባህርያቸው ሳይለወጥ ።

    እንበለ ቡዓዴ ፤ ያለ መለያየት።

    እንደ ጥሬ እህል መለያየት ሳይኖር ከሥጋዌ በኋላ በተዋህዶ ይኖራል ።

    እንበለ ኅድረት ፤ ያለ ማደር።

    እንደ ልብስና ሳጥን ሳይሆን ፤ እንደ እሳትና እንደ ብረት ባለ ተዋሕዶ ።

    እንበለ ትድምርት ፤ ያለ መጨመር።  ዕቃ በዕቃ ላይ እንደሚደራረብና ሲፈለግ እንደሚለያይ ሳይሆን ፤ መለኮቱ ከትስብዕቱ (ከተዋሃደው ነፍስና ሥጋ) ጋር በፍፁም ተዋሕዶ አንድ በመሆን ተወለደ ።

 

ከማን ተወለደ ?

አምላክ የተወለደው ከእመቤታችን ከቅድስተ ቅዱሳን ከንጽህተ ንጹሃን ከድንግል ማርያም ሲሆን ፤ ከሷ እንደሚወለድም ፤ በእግዚአብሔር መነንፈስ በተቃኙ ቅዱሳን አማካኝነት አስቀድሞ ፤ ምሳሌ ተመስሏል ፤ ትንቢት ተነግሯል ።

ምሳሌ

እግዚአብሔር በሴም ድንኳን ይደር ። ዘፍ 9 ፥ 26 ። ድንኳን የእመቤታችን ፤ እግዚአብሔር ሰው የሆነው ጌታ ምሳሌ ።

የአብርሐም ድንኳን ። ዘፍ 10 ፥ 18 ። ድንኳን የእመቤታችን ፤ በአብርሐም ቤት የተስተናገደው እንግዳ የራሱ ጌታ ምሳሌ

የያዕቆብ መሰላል ። ዘፍ 28 ፥12 ። መሰላል የእመቤታችን ፤ በመሰላሉ ላይ የተቀመጠው ንጉሥ የክርስቶስ ምሳሌ ።

የሙሴ ዕፅ ፥ሐመልማልና ነበልባል ። ዘፀ 3 ፥ 2 ። ሐመልማል የእመቤታችን ነበልባል የመለኮት ምሳሌ ። ውዳ ማር ።

የሙሴ ጽላት ። ዘፀ 31 ፥ 18 ። የጽላቱ ማደሪያ የሆነው ታቦት የእመቤታችን ፤ ጽላት የጌታ ምሳሌ ።

የጌዴዎን ፀምርና ጠል ። መሳፍ 6 ፥ 36 ። ፀምር የእመቤታችን ፤ ጠል የጌታ ፤ ምሳሌ ።

 ትንቢት

“ሄዋን ትባል ” ። ዘፍ 2 ፥ 22 ። ሄዋን ማለት እመህያዋን ማለት ነው ። ይህ ስም የተሰጠው ለእመቤታችን ነው ። የመጀ መሪያዋ ሄዋን ሞትን ያመጣች ስትሆን ፤ እመቤታችን ግን የሕይወት ባለቤት የሆነው ጌታ ከእሷ ስለተገኘ መሠረተ ሕይወት የሕይወት መገኛ ብለን እንጠራታለን ። መዝ 45 ፥4 ። ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ ። ልዑል የተባለው አምላክ ሲሆን ፤ ማደሪያው የተባለች ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማህፀኗ ተሸክማ የወለደችው የአምላክ እናት እመቤታችን ናት ።

የተቆለፈች ገነት ። መኃ 4 ፥ 45 ። ይህ እመቤታችን አምላክን በድንግልና መውለዷንና ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን የሚያስረዳ ሲሆን ፤ በተጨማሪም በህዝቅኤ 44 ፥ 1 ። ላይ ያለው ይህን ግልጽ ያደርገዋል ።

 እነሆ ድንግል ወልድን ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ይሉታል። ኢሳ 7 ፥ 14 ። ይህ ቃል በቀጥታ የእመቤታችንን የአምላክ እናትነቷን ይገልጻል ። ድንግል የተባለች እሷ ፤ ወልድ (ልጅ) የተባለ ልጇ አማኑኤል ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና ።

የነቢያት ትንቢት ሲፈጸም ፤ በህጋዊና በተቀደሰ ጋብቻ ከሚኖሩ ኢያቄምና ሐና በብሥራተ መልአክ እመቤታችን እንድት ወለድ አደረገ የተወለደችውም አዳምና ሄዋን ሳይበድሉ በነበራቸውና መርገም (ጥንተ አብሶ የመጀመሪያ በደል) ባልተላለፈበት ንፁህ አካል ነው ። ከእሷ የሚወለደው አምላክ ለባህርዩ ኃጢአት ስለማይስማማው ፤ የሰዎችን ሁሉ በደል ለመቀበልም ንፁህ መሆን ስላለበት ፤ ይህንም ከአምላክ በቀር የሚያሟላ ባለመኖሩ ፤ ከእሷ ሊወለድ ከመርገም ንፁህ እንድትሆን አደረገ ።

እመቤታችን ነሐሴ 7 ተፀንሳ ግንቦት 1 ሊባኖስ በሚባል ቦታ ተወለደች ። ኢያቄምና ሐና የወለዷት በስለት ስለነበረ በተወለደች ከሶስት ዓመቷ ጀምሮ ለ12 ዓመታት ያህል በቤተ መቅደስ አደገች ። 15 ዓመት ሲሆናት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ መጥቶ አምላክን ትውልጃለሽ ብሎ ባበሰራት ጊዜ እንደ ቃልህ ይደረግልኝ ብላ ስትቀበል ቃሏን ምክንያት አድርጎ አምላክ ከሥጋዋና ከነፍሷ ከፍሎ ከመለኮቱ ጋር በማዋሃድ መጋቢት 29 ተፀንሶ ታህሳስ 29 ተወለደ ። በዚህም ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ ሆነ የሃይማኖታችን ስያሜም ኦርቶዶክስ ተዋሕዶመባሉ በዚህ ምክንያት ነው ።

 

የት ተወለደ ?

በሚክያስ 5 ፥2 ። እንደተነገረው ጌታችን የተወለደው በቤተ ልሔም ከተማ በከብቶች በረት ውስጥ ነው ። ህዝቡ ሁሉ እን ዲጻፍ(እንዲቆጠር) ትእዛዝ ተላልፎ ስለነበረ ዮሴፍ እመቤታችንን ይዞ ሊመዘገብ ከናዝሬት ወደ ቤተ ልሔም በሄደበት ወቅት ከህዝቡ ብዛት የተነሳ ቤት አጥተው በከብቶች በረት ተጠግተው አደሩ በዚያም እያሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰና የዓለም መድኃኒት የሆነ ክርስቶስን በድንግልና ወለደች ። ማቴ 1 ፥ 18 ። ሉቃ 2 ፥ 1 ። በተወለደ ጊዜ አስቀድሞ ትንቢት ተነግሮላቸው የነበሩ ሰብአ ሰገል ፤ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ ኮከብ እየመራቸው መጥተው ወድቀው ሰገዱለት ፤ ዕጅ መንሻውንም (ወርቅ ዕጣን ከርቤ) ሰጡት ። ማቴ 2 ፥ 11 ።

በአካባቢው የነበሩ እረኞችም በዙሪያው የሚያበራውን ብርሃን አይተው መልአኩ እየመራቸው ጌታ ከተወለደበት ዋሻ ደር ሰው የጌታን መወለድ አይተዋል ። ከመላእክት ጋር ሆነው

ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር፤ በሰማያት ምስጋና ተደረገ በምድርም ሰላም ሆነ ለሰው ልጅ በጎ ፈቃድ በማለት ዘምረዋል ። ሉቃ 2 ፥ 14 ።

 

3

ምሥጢረ ጥምቀት 

መግቢያ

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስን  “እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” ብሎ እንደተናገረው ከውኃና ከመንፈስ ተወልደን የሥላሴን ልጅነት የምናገኝበት መንግሥተ ሰማያት የምንገባበት ኃጢአታችን የሚደመሰስበት ድኅነትን የምናገኝበት ዐቢይ ምሥጢር ነው /ዮሐ. 3፥5/፡፡ ጥምቀት በምሥጢረ ሥላሴና በምሥጢረ ሥጋዌ አምኖ ለሚፈጽመው ሰው ሁሉ ለኃጢአት መደምሰሻ ከሥላሴ የጸጋ ልጅነት ለመቀበልና የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የተሰጠ ልዩ የሕይወት መንገድ ነው፡፡ ጥምቀት በጽርዕ ቋንቋ ኤጲፋኒያ በግእዝ አስተርዮ በአማርኛ መገለጥ ይባላል፡፡ ቃሉ በቀጥታ ሲተረጎም በውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት፣ መነከር፣ መዘፈቅ፣ መጥለቅ ማለት ነው፡፡ ጥምቀት ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን (ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ሜሮን፣ ምሥጢረ ቁርባን፣ ምሥጢረ ንስሐ፣ ምሥጢረ ክህነት፣ ምሥጢረ ተክሊል፣ ምሥጢረ ቀንዲል) አንዱ ነው፡፡

 

የጥምቀት አመጣጥ

የምሥጢረ ጥምቀት መሥራች ራሱ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ነገር ግን ከጌታችን ጥምቀት በፊት አይሁድ ለመንጻትና ለኃጢአት ሥርየት (ይቅርታ) የሚጠመቁት ጥምቀት ነበራቸው፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር በረድኤት የሚገለጥባቸው የተቀደሱ ዕለታትና ቦታዎች ሁሉ ሰውነትንና ልብስን ማጠብ የእግዚአብሔር ቤት ማገልገያ የሆኑ ዕቃዎችን ሁሉ ማጠብ ማንጻት ሥርዓትና ልማድ ነበር፡፡ የእግዚአብሔርም ፈቃድ ያለበት አሠራር ነበር፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቤት ከመቅረባቸውና ለተቀደሰው አገልግሎት ከመግባታቸው አስቀድመው እግሮቻቸውንና እጆቻቸውን የመታጠብ ግዴታም ነበራቸው፡፡ ሰውነታቸውን ከአፍአዊ (ከውጫዊ) እድፍ በማጠብና ንጹሕ በማድረግ በባሕርይ ንጹሕና ቅዱስ በሆነው አምላክ ፊት ውስጣዊ ሕይወትን ንጹሕ አድርጎ የመቅረብን ሥርዓትና ምሥጢር የሚያመለክት ልማድ ነበር፡፡

 

የጥምቀት ምሳሌዎች

አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ መልከጼዴቅ መሔዱ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም የምእመናን መልከጼዴቅ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ናቸው፡፡ /ዘፍ. 14፥17/

ኢዮብ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ተፈውሷል፡፡ ይህም ምእመናን ተጠምቀው ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ የመፈወሳቸው ምሳሌ ነው፡፡

ንዕማን ሶርያዊ ተጠምቆ ከለምጽ ድኗል፡፡ /2ነገ. 5፥14/ ይኸውም ምእመናን ተጠምቀው ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ የመዳናቸው ምሳሌ ነው፡፡

የኖኅ መርከብ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ. 6፥13 ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍሳት በውኃ የዳኑባትን መርከብ ሲሠራ በኖኅ ዘመን የእግዚአብሔር ትዕግሥት በዘገየ ጊዜ ቀድሞ ክደውት ለነበሩት ሰበከላቸው፡፡ አሁንም እኛን በዚያው አምሳል በጥምቀት ያድነናል ሥጋን ከዕድፍ በመታጠብ አይደለም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመነሣቱ በእግዚአብሔር እንድናምን መልካም ግብርን ያስተምረን ዘንድ ነው እንጂ” /1ጴጥ. 3፥20/

ለአብርሃም ሕግ ሆኖ የተሰጠው ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም ከአረጀ በኋላ ቢገረዝም ልጆቹ ግን በተወለዱ በስምንተኛው ቀን እንዲገረዙ እግዚአብሔር አዞ ነበር /ዘፍ. 17፥9/ “በሰው እጅ የአልተደረገ መገረዝን በእርሱ ሆናችሁ ተገረዛችሁ፡፡ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችኋል በእርስዋም ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትና በሃይማኖት ከእርሱ ጋር ተነሥታችኋል” /ቈላ. 2፥11/

 

ጌታችን ለምን ተጠመቀ?

  1. የዕዳ ደብዳቤያችንን ለመደምሰስ
  2. አዳምና ሔዋን ፍዳው በፀናባቸው መከራው በበዛባቸው ጊዜ የሚያቃልልላቸው መስሏቸው ዲያብሎሰ ስመ ግብርናችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ ባላቸው ጊዜ አዳም ገብሩ ለዲያቢሎስ (አዳም የዲያብሎስ የወንድ አገልጋይ) ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ (ሔዋን የዲያብሎስ ሴት አገልጋይ) ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡ ዲያብሎስም ይህንን ደብዳቤ አንዱን በሲኦል አንዱን በዮርዳኖስ አስቀመጠው፡፡ በዮርዳኖስ ያስቀመጠውን ጌታችን ሲጠመቅ እንደሰውነቱ ረግጦ ደምስሶታል፡፡ ይህንን ጽሕፈት ለመደምሰስ ነው ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀው፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው” ያለው /ቆላ 2፥14/፡፡

  3. ምስጢረ ሥላሴን ለመግለጥ
  4. ጌታችን በፈለገ ዮርዳኖስ ሲጠመቅ ምስጢረ ሥላሴ ግልጽ ሆኗል፡፡ አብ በደመና “የምወደው የምወልደው ልጄ ይህ ነው” በማለቱ አብ የወልድ አባት መሆኑ ታወቀ፡፡ መንፈስ ቅዱስም የባሕርይ ሕይወቱ መሆኑን ሲያስረዳ በአምሳለ ርግብ በራሱ ላይ ተቀመጠ ወልድም በተለየ አካሉ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ታየ፡፡ ስለዚህ ምሥጢርን ለመግለጥ ስንል የአንድነት የሦስትነት ምስጢር በጐላ ሁኔታ እንዲታወቅ ተጠመቀ ማለት ነው፡፡ /ማቴ. 3፥16/

  5. ትንቢቱን ለመፈጸም
  6. “አቤቱ ውሆች አዩህ፣ ውሆችም አይተውህ ፈሩ ጥልቆች ተነዋወጡ ውሆችም ጮኹ፡፡” ተብሎ በቅዱስ ዳዊት የተነገረውን ትንቢት ለመፈጸም ተጠመቀ /መዝ 77፥16/፡፡ጌታችን መቼ ተጠመቀ?ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በ5531 ዓመተ ዓለም ዘመነ ሉቃስ ማክሰኞ ጥር 11 ቀን ከሌሊቱ በ10ኛው ሰዓት ነበር፡፡ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 19 በተጠመቀም ጊዜ ዕድሜው 30 ዓመት ከ13 ቀን ነበር፡፡ /ሉቃ. 3፥23/በብሉይ ኪዳን ሥርዓትና ልማድ ካህናት ለቤተ እግዚአብሔር ተልእኮ እና መንፈሳውያን አገልግሎቶች ከ30 ዓመት ዕድሜ በፊት አደባባይ አይወጡም ነበር፡፡ እጅግ አስፈላጊ እንኳ ቢሆን ከ20 እና 25 ዓመት አስቀድሞ ለአገልግሎት መሰየም ልማድ አልነበረም፡፡

    የቤተ እግዚአብሔር አገልጋዮች በዕድሜና በዕውቀት የበሰሉ፣ በጠባይና በሥራ ልምድ የተፈተኑ ተልዕኳቸውን በብቃት ለመወጣት በተገልጋዩ ሕዝብ ዘንድ የተመሰከረላቸው መሆን ነበረባቸው፡፡ /ዘጸ. 4፥3፤1ዜና መዋ. 23፥24፤ 1ጢሞ. 3፥6-10/ ያንን ሥርዓት ለመፈጸም ጌታችን የተጠመቀውና ለትምህርተ ወንጌል የተገለጠው በ30 ዓመቱ ነበር፡፡ ዮሐንስ መጥምቅም የጌታን መምጣት ለማወጅ በዮርዳኖስ ይሁዳ ምድረ በዳዎች ወጥቶ የታየው ከ30 ዓመት ዕድሜው በኋላ ነው፡፡ ሌላው ዐቢይ ምክንያት የሰው ሁሉ መጀመሪያ አዳም የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ተፈጥሮ በ40ኛ ቀን ተሰጥቶት ኋላም በኃጢአት ምክንያት ያስወሰደውን ልጅነት ለማስመለስ ነው፡፡ ክርስቶስ የተጠመቀው ክብር ሽቶ ሳይሆን የአብ የባሕርይ ልጅነቱን (የባሕርይ አምላክነቱን) ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ለማስመስከር፣ ውኃውን ለመቀደስ፣ የአዳምን ልጆች የእዳ ደብዳቤ ለመደምሰስና በስህተት የጠፋውን የልጅነት ክብር ለመመለስ ነው፡፡

    ጌታ ተጠምቆ ከውኃው ከወጣ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ በማረፍ አብ በደመና “ይህ ልጄ ነው” ብሎ ሲመሰክርለት ምሥጢረ ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በጉልህ ተረጋግጧል፡፡ /ማቴ. 3፥16/

     

የጌታችን ጥምቀት በዮርዳኖስ

በኢየሩሳሌም አካባቢ ብዙ ወንዞች ኩሬዎችና ሐይቆች መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ ጌታ ጥምቀቱን በዮርዳኖስ ያደረገው ስለዚሁ አስቀድሞ የተነገረውን ትንቢት መፈጸሙን ለማረጋገጥ ነው፡፡ “ባሕር አይታ ሸሸች ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ” /መዝ. 113፥3/ ከዚህም ጋር ከላይ ምንጩ አንድ የሆነው ዮርዳኖስ ዝቅ ብሎ በደሴት ተከፍሎ እንደገና እንደሚገናኝ በግዝረት በቁልፈት (በመገዘርና ባለመገዘር) ተለያይተው የነበሩ ሕዝብና አሕዛብ መላው የአዳም ልጆች በጌታችን ጥምቀት አንድ መሆናቸውን የሚገልጽ ትርጉም አለው፡፡

እስራኤል ዮርዳኖስን ተሻግረው ምደረ ርስት ገብተዋል፡፡ ያመኑ የተጠመቁ ምዕመናንም በጥምቀት ገነት መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ፡፡ ሌላው በዮርዳኖስ ተጥሎ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤ ይደመስስልን ዘንድ /ቈላ. 2፥14/

 

4

ምሥጢረ ቁርባን

መግቢያ

ቁርባን ፤ ማለት ፣ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ አምኃ ፣ መስዋዕት ፣ መንፈሳዊ ነገር ሁሉ ማለት ሲሆን ፤ በዚህ ትምሕርታችን ግን ፤ ስለ ሐዲስ ኪዳን መስዋዕት (የክርስቶስ ሥጋና ደም) እንማራለን።

በብሉይ ኪዳን ለሐዲስ ኪዳን ቁርባን (መስዋዕት) ምሳሌዎች

የመልከ ጼዴቅ መስዋዕት ዘፍ 14 ፥ 18 ። ዕብ 5 ፥ 6 ። ዕብ 6 ፥ 1 ። ህብስቱ የሥጋው ፤ ወይኑ የደሙ ምሳሌ ፤ መልከ ጼዴቅ የክርስቶስ ፤ አብርሐም የምዕመናን ።

የእስራኤል ፋሲካ ። ዘፀ 12 ፥ 1 ። ሞት የዲያብሎስ ፤ እስራኤል የምዕመናን ፤ በጉ የክርስቶስ ምሳሌ ።

የእስራኤል መና ። ዘፀ 16 ፥ 13 ። መና የጌታችን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ፤ እስራኤል የምዕመናን ፤ ደመና የእመቤታችን

 

በብሉይ ኪዳን መስዋዕት ቁርባን ያቀረቡና በረከት ያገኙ አባቶች

አዳም አባታችን አዳም ባቀረበው መስዋዕት ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ሰው ሆኖ እንደሚያድነው ቃል ገባለት ። ዘፍ 3 ፥ 22 ። ገላ 4 ፥ 4።

ኖኅ ባቀረበው መስዋዕት ለኖኅና ለልጆቹ ምድርን ዳግም በመቅሰፍት እንደማያጠፋት በቀስተ ደመና ምልክት ቃል ገባላቸው ። ዘፍ 9 ፥ 1 ። ዘፍ 9 ፥ 8።

አብርሐም ዘፍ 18 ፥ 3 ። አባታችን አብርሐም ባቀረበው መስዋዕት በዘርህ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ የሚለውን የተስፋ ቃል ሰማ ፤ ያም ዘር የተባለው ለጊዜው ይስሐቅ ሲሆን፤ ፍጻሜው ግን ለጌታ ነበር ።

መልከ ጼዴቅ ዘፍ 14 ፥ 17 ። መዝ 109 ፥ 4 ። ዕብ 5 ፥ 6 ። በእግዚአብሔር ፊት ባቀረበው መስዋዕት ክህነቱ ለዘለዓለም ተብሎለት የክርስቶስ ምሳሌ ሆነ ። ዕብ 7 ፥ 1 ።

ዳዊት መዝ 131 ፥ 11 ። መስዋዕት ባቀረበበት ሠዓት ከአብራክህ የተገኘው ልጅህ በዙፋንህ ይነግሣል ተባለለት ፤ ይህም ለጊዜው የተነገረው ለሰሎሞን ሲሆን ፍጻሜው ለክርስቶስ ነበር ። መዝ 71 ፡1 ። ሌሎችም በእግዚአብሔር ፊት ንጹህ መስዋዕታ ቸውን እያቀረቡ በረከት ተቀብለዋል።

 

ምሥጢረ ቁርባን በሐዲስ ኪዳን

በብሉይ ኪዳን ዘመን ይቀርብ የነበረው የመስዋዕት ቁርባን ፤ ከበግ ፤ ከላምና ፤ ከተለያዩ እንስሳት ነበር ። በሐዲስ ኪዳን ግን እንስሳት በቤተ መቅደስ ውስጥ መስዋዕት (ቁርባን) ሆነው አይቀርቦም መስዋዕት ሁሉ በክስቶስ ሥጋና ደም ተጠቃሏል ።

ይህንም የአዲስ ኪዳን መስዋዕት የመሠረተው ራሱ ጌታችን ሲሆን ፤ በጸሎተ ሐሙስ ማታ አስራ ሁለቱ ሐዋርያት እንዳሉ በመጀመሪያ መስዋዕተ ኦሪትን ሰርቶ ካሳለፈ በኋላ ኅብስቱና ወይኑን ባርኮ “ነገ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬና የሚፈሰው ደሜ ይህ ነው ብሉ ጠጡ ብሎ ሰጣቸው” ። ማቴ 26 ፥ 26 ።

ዛሬ ካህኑ ኅብስቱን በጻህል ወይኑን በጽዋ አድርጎ ጸሎተ ቅዳሴውን እየጸለየ.. ሲባርከው እንደዚያ ጊዜው ኅብስቱ ተለውጦ ሥጋ መለኮት ወይኑም ተለውጦ ደመ መለኮት ይሆናል ። ይህንም ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም በምንቀበልበት ጊዜ ለእኛ ሲል የተቀበለውን መከራና ስቃይ እያሰብን ራሳችንን በንስሓ ከኃጢአት ንጹህ አድርገን ከንስሓ የቀረውን በደላችንን እንደሚደመስ ስልን ፤ ከበደል እንደሚያነጻንና የዘለዓለም ሕይወት እንደሚሰጠን አምነን መሆን አለበት ።

በ1ቆሮ 11 ፥ 23 “ይህንም ለመታሰቢያዬ አድርጉት ” የሚለው ቃል ሥጋውንና ደሙን በምንቀበልበት ጊዜ ስለሰው ልጆች ሲል በቀራንዮ አደባባይ የተበውን መከራና በልባችን ውስጥ የተሳለውን አምላካዊ ፍቅሩን እያስታወስን እንድንኖር ነው መታሰቢያ የሚለው ቃል የሚያመለክተው የማይረሳ ነገርን ነውና ። ገላ 3፥1

ጌታችን ይህን ምሥጢር ከማሳየቱ (ከመመስረቱ) በፊት በዮሐ 6 ፥ 25-8 ። “ሥጋዬን ካልበላችሁ ደሜንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም ሥጋዬን የበላ ደሜንም የጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ (ሕይወትን የሚሰጥ) ነው ” በማለት ስለምሥጢረ ቁርባን በስፋት አስተምሯል ።

የቅዱስ ቁርባን ጥቅም

ከዚህ ዓለም በሞት ብንለይም እንኳን በሰማያዊ መንግስት የማያልፈውን የዘለዓለም ሕይወት እናገኛለን ። ዮሐ 6 ፥ 54 ።

ለኃጢአታችን ስርየት (ፍጹም ድኅነት) እናገኛለን ። ማቴ 26 ፥ 26 ።

ከጌታችን ጋር ከቅዱሳንም ጋር ያለንን አንድነት እናረጋግጠጣለን ። 1 ቆሮ 10 ፥ 17 ።

ሥጋውን በስንዴ ደሙን በወይን ያደረገበት ምክንያት ትንቢቱንና ምሳሌውን ለመፈጸም ነው

 

ትንቢት

በልቤ ደስታ ጨመርሁ ከስንዴ ፍሬና ከወይን ፍሬ በዛ ። መዝ 4 ፥ 7 ። ይህም ቃል እውነተኛና ፍጹም የሆነው ዘለዓለማዊ መድኃኒት ቅዱስ ቁርባን በስንዴና በወይን እንደሚደረግ ያመለክታል ።

 

ምሳሌ

የክርስቶስ ምሳሌ፤ መልከ ጼዴቅ መስዋዕት የሚያቀርበው በስንዴና በወይን ስለነበረ ምሳሌውን ለመፈጸም ። ዘፍ 14 ፥ 17 ።

ሥጋውንና ደሙን በምግብ ያደረገበት ምክንያት

ምግብ ከሰውነት ጋር እንደሚዋሃድ ሥጋውንና ደሙን ስንቀበል በእውነት እንደሚዋሃደን ለማስረዳት።

ምግብ ለሥጋችን ኃይል እንደሚሆነን ሥጋውና ደሙም ለነፍሳችን መንፈሳዊ ኃይል ይሰጠናል።

አዳምና ሄዋን በምግብ የእግዚአብሔር ልጅነታቸውን እንዳስወሰዱ ፤ በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ልጅነታችንን ሊመልስልን ። ዘፍ 3 ፥ 1 ። ዮሐ 6 ፥ 49።

ቅዱስ ቁርባንን ፤ በበላችን ንስሓ ከገባን በኋላ ሁልጊዜ መቀበል ይገባናል ። የኃጢአታችን ስርየት የሚረጋገጠው በቅዱስ ቁርባን ነውና ። ማቴ 27 ፥ 27።

ምዕመናን በሕይወት እስካሉ ደረስ ወንድም ይሁን ሴት ፣ ታናሽም ይሁን ታላቅ ከቅዱስ ቁርባን መለየት የለባቸውም ይህ ምሥጢር በፆታ በዕድሜ የማይገደብ ለሁሉ የተሰጠ ነውና ። ዮሐ 6 ፥ 54 ። በሰራነው ስህተት ተጸጽተን ንስሓ ሳንገባ በድፍረት ሥጋውንና ደሙን መቀበል የለብንም ፤ ይህን የሚያደርጉ ሰዎች ዕዳ አለባቸው ። 1ቆሮ 11 ፥ 27 ። የምንቀበለው ቅዱስ ቁርባን ጌታችን በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ ከዋለ በኋላ ፤ ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን በራሱ ሥልጣን ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለይቷል ። ዮሐ 10 ፥ 18 ። ዮሐ 19 ፥ 30 ። በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ሄዶ በዚያ የነበሩ ነፍሳትን ወደ ገነት ከመለሰ በኋላ ሶስት መዓልትና ሶስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ከነበረው ሥጋ ጋር በፈቃዱ አዋህዶ ተነሳ ፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ግን(ሥጋውና ደሙ በተለያዩበት ወቅት) መለኮት ፣ ከነፍ ስም ከሥጋም ጋር አልተለየም ። 1ዼጥ ። ስለዚህ እኛ የምንቀበለው ሥጋና ደም ፤ ነፍስ የተለየችው መለኮት የተዋሃደው ነው ። 1ዼጥ 3 ፥ 18 ።

5

ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን

የጌታችን ትንሣኤ

ስለ ጌታችን ሞትና ትንሣኤ የተነገረ ትንቢት ፤ የተመሰለ ምሳሌ ትንቢት

እኔ ተኛሁ አንቀላፋሁ ፤ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርነቴ) ደግፎኛልና ነቃሁ ። መዝ 3 ፥ 5 ።

እግዚአብሔር ይነሣ ፤ ጠላቶቹም ይበተኑ ፤ የሚጠሉትም ከፊቱ ይሽሹ ። መዝ 27 ፥ 1 ።

እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሳ ። መዝ 77 ፥ 65።

ምሳሌ

ዮናስ ፤ ሶስት ቀንና ሶስት ሌሊት በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ማደሩ ፤ ለጌታችን ሞትና ትንሣኤ ምሳሌ ፤ እንደነበረ ጌታችን ተናግሯል ። ዮና 3 ፥ 1 ። ማቴ 12 ፥ 40 ።

በዮርዳኖስ ባህር ውስጥ ገብቶ መጠመቁ የሞቱ ፤ ከባህር መውጣቱ የትንሣኤው ምሳሌ ነበር ።

ጌታችን ዓርብ ከቀኑ በዘጠኝ ሠዓት ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በፈቃዱ ከለየ በኋላ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከዺላጦስ አስፈቅደው ዮሴፍ ለራሱ ባዘጋጃት መቃብር ከቀኑ በ11 ሠዓት ቀበሩት ።

ሥጋው ሶስት መዓልትና ሶስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ሲቆይ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ሄዶ በግዞት የነበሩ ነፍሳትን (አዳምን ከነልጆቹ) ወደ ቀደመ ቦታቸው ከመለሰ በኋላ ቅድስት ነፍሱንና ቅዱስ ሥጋውን በፈቃዱ አዋሕዶ ቅዳሜ ማታ ለእሑድ አጥቢያ ከሌሊቱ በ6 ሠዓት ተነሳ። መለኮት ግን(ሳይከፈል) ከነፍስ ጋር በሲኦል ፤ ከሥጋ (በመቃብር) ጋር አልተለየም ። ጌታችን በአካለ ነፍስ በሲኦል የቆየው (ዓርብ ከቀኑ ዘጠኝ ሠዓት እስከ ቅዳሜ ሌሊት ስድስት ሠዓት) ለ32 ሠዓታት ያህል ነው ። በሥጋው 33 ዓመታት በምድር ፤ ነፍሱ ከሥጋው እስክትዋሃደችበትና እስከተነሳበት ጊዜ 33 ሠዓታት በሲኦል መቆየቱን እንረዳለ ።

ጌታችን ሶስት ቀንና ሌሊት በመቃብር ቆየ ማለት ዓርብ ከአስራ አንድ ሠዓት በኋላ ያለው እንደ ሃያ አራት ሠዓት ተቆጥሮ አንድ ቀንና ሌሊት ሲባል ፤ ዓርብ ማታና ቅዳሜ ቀን ሁለተኛ ቀንና ሌሊት ፤ የቅዳሜ ሌሊት ስድስቱ ሠዓት ከእሑድ ቀን ጋር ተቆጥሮ ሶስተኛ ቀንና ሌሊት ይሆናል።

ይህም በባህረ ሐሳብ ትምህርት መዓልት ይስህቦ ለሌሊት ፤ ወሌሊት ይስህቦ ለመዓልት ። ቀን ሌሊትን ፤ ሌሊትም ቀን ፤(የኋለኛው የፊተኛውን ፤ የፊተኛው የኋለኛውን) ይስበዋል ፤ በሚለው አቆጣጠር ነው።

የጌታችን ትንሣኤ ለሰዎች ትንሣኤ አብሳሪ(በኩር) ነው ። 1 ቆሮ 15 ፥ 20 ። እኛም እንደ እሱ ባለ ሞት (እርሱን በማመን ፀንተን) ከሞትን እንደ እርሱ ባለ የክብር ትንሣኤ ያስነሳናል ። ሮሜ 6፥5 ። ጌታችን ቅዳሜ ሌሊት ለእሑድ አጥቢያ ከከሌሊቱ በ6 ሠዓት ከተነሳ በኋላ ለሐዋርያት ሶስት ቀን ተገልጾላቸዋል ።

ይኸውም

በተነሳበት ቀን እሑድ ከቀኑ በ11 ሠዓት ደቀ መዛሙርቱ በዝግ ቤት ወስጥ ተቀምጠው እያሉ ተገለጠላቸው ። ሉቃ 24 ፥ 36 ። ዮሐ 20 ፥ 19 ።

በተነሳ በሳምንቱ እንደዚሁ በዝግ ቤት ውስጥ እንዳሉ ሰላም ለእናንተ ይሁን ብሎ በድጋሚ ተገለጠላቸው ። ዮሐ 20 ፥ 26።

በተነሳ በ25ኛው ቀን (ርክበ-ካህናት) ለሶስተኛ ጊዜ በጥብርያዶስ ባህር አጠገብ ተገልጦ ከእነሱ ጋር ማዕድ በላ ። ዮሐ 21 ፥ 1-14።

በነዚህ ጊዜያት ውስጥ ሰባቱን ኪዳናት እያስተማራቸው ከቆየ በኋላ ፤ መንፈስ ቅዱስን እስክልክላችሁ በኢየሩሳሌም ቆዩ ብሏቸው በአርባኛው ቀን በቢታንያ አደባባይ እያዩት ወደ ሰማይ ዐረገ ፤ በአምሳኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ላከላቸው ።

2  የሰው ልጆች ትንሣኤ

የሰው ልጆች ሁሉም ከዚህ ዓለም በሞት ይለያሉ ። ይሁንና እግዚአብሔር የወሰናት የምጽዓት (የዓለም ፍጻሜ) ቀን ስትደርስ ሁሉም ሰዎች ከሙታንነታቸው ህያዋን ሆነው ይነሳሉ ። ሲነሱ እኩሌቶቹ (ጻድቃን) ለክብር ፤ እኩሌቶቹ (ኃጥዓን)ለፍርድ(በሰሩት ክፉ ሥራ ሊፈረድባቸው) ነው ። ዮሐ 5 ፥ 29 ።

ስለ ሰው ልጆች ትንሣኤ አስቀድሞ ትንቢት ተነግሯል፥ ምሳሌ ተመስሏል

ትንቢት

ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ ፤ ሬሳዎችም ይነሳሉ ፤ ምድርም ሕያዋንን ታወጣለችና ። ኢሳ 26 ፥ 19 ።

በምድርም ዙሪያ ካንቀላፉት ብዙዎች ይነቃሉ ፤ እኩሌቶቹ ወደ ዘለዓለም ሕይወት እኩሌቶቹ ወደ ዘለዓለም ሀፍረትና ጉስቁልና ይሄዳሉ ። ዳን 12 ፥ 1 – 3 ።

እርሱ ሰብሮናልና ይጠግነናል ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል ፤ በሶስተኛውም ቀን ያስነሳናል ። ሆሴ 6፥2 ።

ምሳሌ

የአቤል ሞት ለሞታችን ። ዘፍ 4፥ 8 ። የሄኖክ ዕርገት ለትንሣኤያችን ። ምሳሌ ነው ። ዘፍ 5 ፥ 24 ።

እስራኤል ወደ ግብጽ መውረዳቸው ለሞታችን ። ዘፍ 46 ፥ 1 ። ከግብጽ ወጥተው ከነዓን መግባታቸው ለትንሣኤያችን ምሳሌ ነው ። ግብጽ የመቃብር ፤ ከነዓን የትንሣኤ (የመንግስተ ሰማያት) ምሳሌ ናትና ። ዘፀ 14 ፥ 21 ።

የአልዓዛር ሞቱ ለሞታችን ፤ በአራተኛው ቀን መነሳቱ ለትንሳኤያችን ምሳሌ ነው ። ዮሐ 11 ፥ 1- 44 ። ሌሎችም ትንሣኤ ሙታንን የሚያመለክቱ በርካታ ምሳሌዎች አሉ ።

ሰው የተፈጠረው እንዲሞት ሳይሆን በሕይወት እንዲኖር ነበር ። ይሁን እንጅ በቃኝን በማያውቀው ፍላጎቱ የተሰጠው ሥልጣን አልበቃ ብሎት በዕባብ ውስጥ ባደረው በሰይጣን ምክር ተታሎ ፤ ያልተሰጠውን አምላክነት ሲፈልግ በመገኘቱ ሞት ተፈረደበት ። በአንዱ ሰው አዳም በደል ምክንያትም ሞት ወደ ዓለም መጣ ። ሮሜ 5 ፥ 12 ። በአዳምና በልጆቹ (በሰው ዘር ሁሉ) ላይ የተፈረደው የሞት ፍርድ ሁለት ማለትም ሞተ ነፍስና (ወደ ገሃነም መውረድ) ሞተ ሥጋ (ወደ መቃብር መውረድ) ሲሆን ሞተ ነፍስ አምላካችን ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ ባፈሰሰው ደሙና በቆረሰው ሥጋው ስለተደ መሰሰ አምነው ከተጠመቁ በኋላ ይህን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ለሚቀበሉ ምዕመናን ቀርቶላቸዋል ። የሥጋ ሞት ግን ሁሉም ሰዎች እስኪጠናቀቁ ግዛቱ ይቀጥላል ፤ ሁሉንም ይገዛ ዘንድ ሥልጣን ተሰጥቶታልና ። 1 ቆሮ 15 ፥ 26 ።

 

የሙታን አነሳስ

ሙታን ከመነሳታቸው በፊት መልአኩ 3 ጊዜ የመለከት አዋጅ (ንፍሐተ ቀርን) ያሰማል ። 1 ተሰ 4 ፥ 16

በመጀመሪያው (ንፍሐተ ቀርን) የመለከት ድምጽ የሞቱ ሰዎች አጠቃላይ የሰውነት ክፍላቸው በሙሉ ይሰባሰባል ።

በሁለተኛው የመለከት አዋጅ ፦ የሰውነት ክፍሎቻቸው ከደምና ከሥጋ ጋር ተገጣጥመው የማይንቀሳቀስ በድን ይሆናሉ።

በሶስተኛው የመለከት አዋጅ ፦ የሰው ልጆች ሁሉ በሕይወት ዘመናቸው የሠሩትን መልካምም ሆነ ክፉ ሥራቸውን ይዘው ፤ ወንዶች የሰላሳ ፤ ሴቶች የአስራ አምስት ዓመት ዕድሜ ያህል ሆነው ይነሳሉ ። ሲነሱም ጻድቃን ፈጣሪያቸውን ክርስቶስን መስለው ፤ ኃጥዓንም አለቃቸውን ዲያብሎስን መስለው ይነሳሉ ።

ከዚህ በኋላ ጌታችን በክበበ ትስብዕት (በለበሰው ሥጋ እየታየ) በግርማ መነግሥት (በሚያስፈራ የመለኮት ግርማ) ሆኖ በመላእክት ታጅቦ የተሰቀለበትን መስቀል ፊት ለፊቱ አደርጎ ይመጣል ። መስቀል የፍርድ ምልክት ነውና በዚህ ጊዜ በቀራንዮ አደባባይ በግፍ ሰቅለው የገደሉት አይሑድ ያፍራሉ ። ማቴ 25፥31።

ጌታችን ፤ ጻድቃንን በበግ ፥ ኃጥዓንን በፍየል ይመስላቸዋል

ይህም ማለት የሰውነት ባህርያቸው ተለውጦ በጎችና ፍየሎች ይሆናሉ ማለት ሳይሆን በሕይወት ዘመናቸው በዚህ ዓለም ሲኖሩ የሰሩት ሥራቸው በበጎችና በፍየሎች ምሳሌ ሆኖ ስለቀረበ ያንኑ ለማስረዳት ነው ።

በጎች፦ እረኛቸው ባሰማራቸው ቦታ ረግተው ይውላሉ፤ ጻድቃንም እውነተኛ እረኛቸው ክርስቶስ በሰራላቸው ህግ ጸንተው ይኖራሉና ። ዮሐ 10 ፥ 1 ። ዮሐ 21 ፥ 15 ።

ፍየሎች ፦ ለእረኛ አስቸጋሪዎች ናቸው ፣ በአንድ ቦታ መርጋትም አይችሉም ። ኃጥዓንም በተፈቀደላቸው ህግ አይኖሩም ወረተኞች ቀላዋጮች ናቸው ።

በጎች ፦ ጥቂት ሳር ካገኙ ተስማምተው ይበላሉ ። ጻድቃንም ኑሮዬ ይበቃኛል ፡ በማለት ያለቻቸውን ከድሆች ጋር ተካፍለው ይበላሉ ።

ፍየሎች ፦ የሚበሉት ሳሩ ቅጠሉ እያለ እርስ በእርሳቸው ሲጣሉ ፤ ሲያጉረመርሙ ይውላሉ ። ኃጥዓንም ሁሉ እያላቸው ሲጣሉ ሲካሰሱ ፤ ሲገዳደሉ ፤ የሌላውን ሲመኙ ፤ ሲሰርቁ ፤ ይኖራሉ ።

የበጎች ፦ ኀፍረተ ሥጋቸው በላታቸው የተሸፈነ ነው ። የጻድቃንም ኃጢዓታቸው በንስሓ የተሰወረ ነው ።

የፍየሎች ፦ ኀፍረተ ሥጋቸው የተገለጠ ፤ ላታቸው የተሰቀለ ነው ። ኃጥዓንም ነውራቸው ለሁሉ የተገለጠ ኀፍረት የሌላቸው ደፋሮች ፤ በነውራቸውና በክፉ ሥራቸው የሚመኩና የሚኩራሩ ፤ ናቸው ።

በጎች ፦ ሲሄዱ አንገታቸውን ወደ ታች አቀርቅረው ነው ፤ ጻድቃንም ሲኖሩ አንገታቸውን ደፍተው ራሳቸውንዝቅ አድርገው በትህትና ነው ።

ፍየሎች፦ ሲሄዱ አንገታቸውን አቅንተው ሽቅብ እያዩ ነው ፤ ኃጥዓንም ሲኖሩ ከአቅማቸው በላይ በማሰብ በትዕቢት ተወጥረው ፤ ከእኛ በላይ አዋቂ ለኀሳር እያሉ የሌላውን ሥራ በማኮሰስ ነው ።

በጎች ፦ ከጓደኛቸው አንዱን ተኩላ ፡ ቀበሮ ፡ ከበላባቸው ፡ አካባቢውን ለቀው ይሄዳሉ ፡ በረው ይጠፋሉ ። ጻድቃንም ከመካከላቸው አንዱ በሞት ቢነጠቅ ነገም ለእኛ ብለው ራሳቸውን ለንስሐ ያዘጃሉ

ፍየሎች ፦ ከጓደኛቸው አንዱን አውሬ ቢነጥቀው ለጊዜው ዘወር ይሉና ፥ በኋላ ረስተውት ተመልሰው በአካባቢው ሳሩን ቅጠሉን ሲበሉ ይገኛሉ ። ኃጥዓንም ከመካከላቸው አንዱ በሞት ሲነጠቅ ለጊዜው ያዘኑ ይመስሉና ጥቂት ቆይተው የሞተውን ሰውዬ ረስተውት ፤ ጥሎት በሄደው በሃብቱና በንብረቱ ሲጣሉ ሲካሰሱ ይታያሉ ።

ጌታችን ለፍርድ ሲቀመጥ ጻድቃንን በቀኙ ኃጥዓንን በግራው ያቆማቸዋል ። ማቴ 25 ፥ 31 ።

 

ምሳሌነቱም :-

ቀኝ ፈጣን ነው ። ጻድቃንም ለበጎ ሥራ ፈጣኖች ፡ ትጉኃን ናቸውና ።

ግራ ዳተኛ ነው ። ኃጥዓንም ለመልካም ነገር ዳተኞች ናቸው ፤ አይመቻቸውም ።

ቀኝ ከግራ ይልቅ ጠንካራ ነው ። ጻድቃንም ለበጎ ሥራ ብርቱዎች ናቸው ።

ግራ ከቀኝ ይደክማል ። ኃጥዓንም ጹሙ ጸልዩ ሲባሉ ፣ አይችሉም ይሰንፋሉ ።

ቀኝ ለሥራ ይመቻል ቀና ነው ። ጻድቃንም ለበጎ ነገር ቅኖች ናቸውና ።

ግራ ጠማማ ነው ለሥራ ብዙም አይመችም ። ኃጥዓንም ሃሳባቸው የተወላገደ ፤ በቃላቸው የማይገኙ ፤ በባህርያቸው ተለዋዋጮች ናቸው ።

ጌታችን ለፍርድ የሚመጣባት ቀን መቼ እንደሆነች ማንም አያውቃትም ። በማቴ 24 ፥ 36 ። ወልድም ቢሆን አያውቃትም የሚለው ግን በእግዚአብሔር የሶስትነት (ከዊን ኩነት) ሁኔታ ውስጥ ፤ አብ ልብ ስለሆነ ፤ በአብ ልብነት ዓለም እንደምታልፍ ታስባለች ፤ ትታወቃለች ። ወልድ ቃል ስለሆነ ፡ ትለፍ ብሎ በቃልነቱ አላወቃትም ፤ ተናግሮ አላሳለፋትም ፤ በድርጊት አልፈጸማትም ማለት ነው ። ከትንሣኤ ሙታን በኋላ ፤ ሰማይ (ጠፈር) ፤ ሶስቱ ሰማያት ፤ ኢዮር ፤ ራማ ፤ ኤረር ፤ ሲኦል ፤ ገነት ፤ አራቱ ባህርያት ፤ መሬት ፤ ውሃ ፤ እሳት ፤ ነፋስ ፤ እንስሳት ፤ አራዊት ፤ አእዋፍ ፤ ያልፋሉ ። ብርሃንና ጨለማ አያልፉም ከ24 ሰዓት ውስጥ ሌሊቱ /ጨለማ ወደ ገሃነመ እሳት ፤ ቀኑ /ብርሃን ወደ መንግስተ ሰማያት ይጠቃለላሉ ። አራቱ ሰማያት ፤ ጽርሐ አርያም ፤ መንበረ መንግስት ፤ ሰማይ ውዱድ ፤ መንግስተ ሰማያት ፤ (ኢየሩሳሌም ሰማያዊት) ፤ ገሐነመ እሳት ፤ ግን አያልፉም ፤ ለዘለዓለም ይኖራሉ ። ማቴ 24 ፡35

በመጨረሻም ጻድቃንን “እናንት የአባቴ ቡሩካን ወደ እኔ ኑ” ብሎ ከቅዱሳን መላእክት ጋር መንግስተ ሰማያትን ያወርሳቸዋል ። ማቴ 22፥30 ። ኃጥዓንንም “እናንተ ርጉማን ለሰይጣንና ለመልእክተኞቹ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘለዓለም እሳት ከእኔ ሂዱ” ይላቸዋል ። ከዚህ በኋላ የዘለዓለም መኖሪያቸው ከግብር አባታቸው ከዲያብሎስና ከአጋንንት ጋር የፍርድና የስቃይ ቦታ በሆ ነው በገሐነመ እሳት ይሆናል ። ራዕ 12 ፥ 7።

በመንግስተ ሰማያት የሚኖሩ ጻድቃን በምድራዊ ሕይወታቸው እያሉ በሠሩት ሥራ የተለያየ ክብር ቢኖራቸውም ፤ በሥልጣን ግን አንዱ ከአንዱ አይበልጥም አንዱ ሌላውን አያዝዘውም ። 1 ቆሮ 15፥41 ።

ሙታን የሚነሱት በማይፈርስ ፤ በማያረጅ ፤ በማይራብ ፥ በማይደክም ፤ በማይሞት ፤ ሥጋ ነው ። 1 ቆሮ 15 ፤ 42 ። በመንግስተ ሰማያት ፤ ጋብቻ የለም ፤ ሁሉም በዚህ ዓለም ያበቃል ። ማቴ 22 ፥ 30 ።